የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ በሰላም እንዲካሄድ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የተለየ ዝግጅት ተደርጓል

ጥር 19/2014 (ዋልታ) የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ በሰላም እንዲካሄድ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የተለየ ዝግጅት መደረጉን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ።

የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ በየዓመቱ የኅብረቱ ዋና መቀመጫ በሆነችው አዲስ አበባ  የሚካሄድ ሲሆን ይሁንና ባለፉት ሁለት ዓመታት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ጉባኤውን በአካል ማካሄድ አልተቻለም፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ ለኢዜአ እንደገለጹት ጉባኤው በሰላም እንዲካሄድ ከኮሚሽኑ አመራሮች ጀምሮ እስከታችኛው መዋቅር ድረስ ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ዝግጅት ተደርጓል።

ጉባኤው በኢትዮጵያ እንዳይካሄድ ሲደረግ ከነበረው ጫና አንጻር የጸጥታ መዋቅሩ በተለየ እልህና ቁጭት ለጉባኤው ሰላማዊነት ከፍተኛ ዝግጅት ማድረጉንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በርካታ ኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራዎች ወደ አገር ቤት በመምጣት ኢትዮጵያ ሰላም መሆኗን በተግባር እንዳረጋገጡ አንስተው ዳያስፖራዎቹ ያለምንም የጸጥታ ችግር የገና እና ጥምቀት በዓላትን እንዲያከብሩ ፖሊስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አንስተዋል፡፡

ከዚህ አኳያ ፖሊስ የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ በሰላም እንዲከናወን ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚያደርግም ነው የተናገሩት፡፡

ኅብረተሰቡም እንግዶቹን በተለመደ ኢትዮጵያዊ ጨዋነት እንዲያስተናግድም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ጉባኤውን እንደምቹ አጋጣሚ በመውሰድ ህገ-ወጥ የገንዘብ ምንዛሬ ለመስራት የሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ ፖሊስ ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚያደርግ ያሳሰቡት ኮማንደር ፋሲካው ኅብረተሰቡ የሚጠበቅበትን ተሳትፎ በማድረግ ለጉባኤው ስኬት የሚጠበቅበትን ሚና እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል፡፡