የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ዛሬ ይመረቃል

ሰኔ 19/2013 (ዋልታ) – በ40 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው እና በ2 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ወጪ የተገነባው የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) እና በሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ዛሬ ይመረቃል።
አካዳሚው በሱሉልታ አካባቢ የሚገኘውና በቀድሞ አጠራር የመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ ይሠኝ የነበረ ሲሆን፣ ሁሉን አካታች ያልነበረ ስያሜ በመሆኑ እንዲቀየር ተደርጓል።
በ2 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር የተገነባው አካዳሚው 722 ሚሊየን ብር በኢትዮጵያ መንግስት የተሸፈነ ሲሆን፣ ቀሪው ገንዘብ ከቻይና ህዝብ እና መንግስት ድጋፍ የተገነባ ነው ተብሏል።
አካዳሚው እጅግ ዘመናዊ የሆነ እና ሁሉን አካታች ያደረገ፣ 600 ሰው በአንድ ጊዜ መያዝ የሚችል አዳራሽ ያለው እንዲሁም ደረጃውን የጠበቀ 150 ባለ አምስት ኮከብ ማረፊያ ወይም መኝታ ክፍል ያካተተ መሆኑ ተገልጿል።
ዘመናዊ መሳሪያ የተገጠመለት የመሰብሰቢያ አዳራሽም አለው ተብሏል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይአህመድ ልክ እንደ ሸገር ፓርክ፣ እንጦጦ እና ሌሎችም ፕሮጀክቶች ትኩረት ሰጥተው ሲከታተሉት እንደነበር ተገልጿል።
ግንባታው እ.አ.አ በ2019 ተጀምሮ ከስድስት ወር በፊት የተጠናቀቀ ቢሆንም፤ ባለፉት ጊዜያት ሀገር ውስጥ በተከሠቱ የተለያዩ ችግሮች ምክንያት ለምረቃ ሳይበቃ ቆይቶ በዛሬው እለት ለምረቃ በቅቷል።
(በሜሮን መስፍን)