የአፍሪካ አኅጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና የአኅጉሪቱን ንግድ እንቅስቃሴ እንደሚለውጥ ተጠቆመ

መጋቢት 29/2014 (ዋልታ) የአፍሪካ አኅጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና በትክክለኛው መንገድ ከተተገበረ በአኅጉሪቱ ያለውን የንግድ እንቅስቃሴ የመለወጥ አቅም እንዳለው የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ሚኒስትሯ በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የአፍሪካ ነጻ የገበያ ቀጣና ይዞ የመጣው ጥቅም፣ የትራንስፖርት ወጪን በመቀነስና ማሳደግ በሚል ባዘጋጀው የበይነ መረብ ስብሰባ ላይ ተሳትፈዋል፡፡

ከቀጣናዊ ንግድ ጋር በተገናኘ በቅርብ ጊዜያት ለውጥ አለ ያሉት ሚኒስትሯ ከሌሎች ዓለማት ጋር ሲነጻጸር ግን አፍሪካ ወደ ኋላ መቅረቷን በማመልከት የአፍሪካ አኅጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ትግበራ ስኬታማነት ይህን ክፍተት የሚሞላ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡

የአፍሪካ አኅጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና በመላው የአፍሪካ አኅጉር ኢኮኖሚውን በማሳደግ፣ የንግድ እና ሥራ ፈጠራን በማሻሻል ለሸቀጦች እና አገልግሎቶች አንድ የንግድ ማዕከል በመገንባት ድህነትን በመቀነስ ረገድ ለውጥ ያመጣል ተብሎ እንደሚጠበቅም አመላክተዋል፡፡

አክለውም የአፍሪካ አኅጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣናን በመቀላቀል ከትሩፋቱ እንዳይደቋሱ እንቅፋት ነው ያላቸውን የትራንስፖርት መሠረተ ልማት እና የሎጂስቲክስ ችግሮችን ማንሳታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።

የአፍሪካ አኅጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ከአፍሪካ ኅብረት አጀንዳ 2063 ዋነኛ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ነው።