የአፍሪካ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች አዲስ አበባ እየገቡ ነው

ጥቅምት 03/2013 (ዋልታ) ነገ በሚካሄደው 39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ጉባዔ ለመታደም የአፍሪካ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች አዲስ አበባ እየገቡ ነው።

የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ፣ የኮትዲቯር ሪፐብሊክ፣ የጋቦን እና የቡርኪናፋሶ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በዛሬው እለት አዲስ አበባ ገብተዋል።

ሚኒስትሮቹን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፕሮቶኮል ጉዳዮች ዳይሬክተር ፋይሰል አሊይ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

የላይቤሪያ፣ ኒጀር፣ ሴራሊዮን፣ ቡሩንዲ እና አልጄሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በስብሰባው ለመሳተፍ ትናንት አዲስ አበባ ገብተዋል።

39ኛው የኅብረቱ ስራ አስፈጻሚ ምክር ቤቱ መደበኛ ጉባዔ ለሁለት ቀናት “ጥበብ፣ ባህልና ቅርስን የምንፈልጋትን አፍሪካ ለመገንባት እንጠቀም” በሚል መሪ ሃሳብ ይካሄዳል።

በ39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ የሕብረቱ 55 አባል አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እንደሚሳተፉ ከሚኒስቴሩ ቃልአቀባይ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡