የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅ ካሜሩን የሶስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቀቀች

ጥር 29/2014 (ዋልታ) የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅ ካሜሩን በትናንትናው ዕለት በተካሄደው ጨዋታ በፍፁም ቅጣት ምት ቡርኪናፋሶን በመርታት ሶስተኛ ሆና አጠናቃለች።
ካሜሩን በቡርኪናፋሶ 3ለ0 እየተመራች የነበረ ቢሆንም በኋላ ላይ 3 ጎል በማስቆጠር እኩል በመሆናቸው ጨዋታው በፍፁም ቅጣት እንዲጠናቀቅ ሆኗል። በዚህም ካሜሩን አሸናፊ ሆናለች።
ቡርኪናፋሶ በስቲቭ ያጎ፣ የካሜሩኑ አንድሬ ኦናና በራሱ ላይ ባስቆጠራት ግብ እንዲሁም በጅብሪል ኦታራ ባስቆጠሯቸው ጎሎች 3 ለ 0 እየመራች የነበር ቢሆንም በደጋፊዎቻቸው ፊት የተጫወቱት ካሜሩኖች በስቴፋን ባሆከንና በቪንሰንት አቡበከር ሁለት ጎሎች ወደ መጨረሻው ሰዓት እኩል ልትሆን ችላለች።
የጨዋታው 90 ደቂቃ ከተጠናቀቀ በኋላ ተጨማሪ ጊዜ ሳይጨመር ቡድኖቹ በፍፁም ቅጣት ምት እንዲለያዩ ተደርጓል።
ለ49 ደቂቃዎች ያህል ጨዋታውን ተቆጣጥረውት ለነበረው ቡርኪናፋሶዎች ውጤቱ አሳዛኝ ሆኗል።
በተቃራኒው አምስት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊዋ ካሜሩን አምስቱንም የቅጣት ምቶች ወደ ጎል በመቀየር ግሩም በሆነ መልኩ በሶስተኛነት አጠናቃለች።
በዛሬው ዕለት የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ የሚጠናቀቅ ሲሆን የሰባት ጊዜ ሻምፒዮናዋና ክብረ ወሰንን የጨበጠችው ግብፅ የፍፃሜ ጨዋታዋን ከሴኔጋል ጋር እንደምታደርግ ቢቢሲ ዘግቧል።