የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ መጠቀም እምነትን አይሸረሽርም ሲል የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ገለጸ፡፡
ጉባዔው የከተራና የጥምቀት በአላት ሲከበሩ የኮቪድ-19 መከላከያ ዘዴዎች እየተተገበሩ መሆን እንዳለበት እና በዓላቱ በሰላማዊ መንገድ እንዲከበሩ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቋል፡፡
የከተራና ጥምቀት በዓላት ሲከበሩ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በማያስፋፋ መልኩ እንዲሆን ያሳሰበው ጉባዔው፣ ምዕመናኑ በዓላቱን ለማክበር ሲወጣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ መጠቀምን በግዴታነት መውሰድ አለበት፤ ሰላምታውም ቢሆን ምንም አይነት ንክኪ ሊኖረው እንደማይገባ ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጠቅላይ ፀሐፊ ቀሲስ ሊቀ ትጉሀን ታጋይ ታደለ ምዕመናን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ መግዛት አቅም ለሌላቸው ሰዎችም ድጋፍ እያደረገ በዓሉን እንዲያከብር ተናግረዋል፡፡
ቀሲስ ታጋይ እምነቴ ያድነኛል በሚል ምክንያት ማስክ ለማያደርጉ ሰዎችም “የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ መጠቀም እምነትን አይሸረሽርም” ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በአሉ ሲከበር የሰላምና ጸጥታ ጉዳይ ሊታሰብበት ይገባል ያሉት ቀሲስ ታጋይ፣ ኃይማኖትን ሽፋን አድርገው ፖለቲካዊ ጠቀሜታን ለማግኘት በህዝብ መሀከል ግጭትን ለመፍጠር ለሚጥሩ አካላትም ምዕመናኑ ሊነቃባቸው ይገባል ብለዋል፡፡
የከተራ በዓል በነገው እለት ሲከበር፣ የጥምቀት በዓል ደግሞ ከነገ በስትያ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት የሚከበር በዓል ነው፡፡
በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የሚያዘው ሰው ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በቫይረሱ ተጠቅተው በጽኑ ህሙማን ክፍል የሚገኙትም ከቀን ወደ ቀን እየጨመሩ መሆናቸውን የጤና ሚኒስቴር ሪፖርት ያመለክታል፡፡
(በመስከረም ቸርነት)