የአፍዴራ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ የአካባቢውን አየር ንብረት መሰረት አድርጎ መገንባቱ ተገለጸ

ግንቦት 29/2014 (ዋልታ) በአፋር ክልል የተገነባው የአፍዴራ ባለ 230 ኪሎ ቮልት ከፍተኛ ዘመናዊ ማከፋፈያ ጣቢያ የአካባቢውን አየር ንብረት ታሳቢ ያደረገ መሆኑን የፕሮጀክቱ የሳይት ሥራ አስኪያጅ ታምሩ ባቱ ገለፁ፡፡

ስራ አስኪያጁ እንደተናገሩት ማከፋፈያ ጣቢያው በአካባቢው ያለውን ከፍተኛ ሙቀት ተቋቁሞ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ ከዲዛይን አንስቶ በከፍተኛ ጥንቃቄ እና ጥራት ተገንብቷል፡፡

የማከፋፈያ ጣቢያውን ትራንስፎርመር እና ጂ.አይ.ኤስ (GIS) ሲስተሙን ሙሉ ለሙሉ በቤት ውስጥ በማስቀመጥ ደረጀውን የጠበቀ የማቀዥቀዣ ሥርዓት እንዲኖረው መደረጉን ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡

ለማከፋፈያ ጣቢያው ብቻ የሚያገለግል 392 ኪሎዋት ከፀሐይ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚችሉ 60 የፀሐይ ኃይል መሰብሰቢያ ፓኔሎች እንደተገጠሙለትም ገልፀዋል፡፡

ይህም በማከፋፈያው ጣቢያው የናፍጣ ጀነሬተር ስለማይኖር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የነዳጅ ወጪ ከማስቀረቱም ባሻገር የማያቋጥ ኃይል እንዲያገኝ ያስችለዋል ብለዋል፡፡

የሠራተኞች መኖሪያ ቤትም የሠራተኞቹን ምቾት እንዲጠብቁ ሙቀትን ሊቋቋሙ ከሚችሉ የግንባታ ግብዓቶች መገንባታቸውንና በቂ የማቀዥቀዣ ሲስተም እንዲኖረው መደረጉን ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል፡፡

ከሠራተኞች መኖሪያ ቤት በተጨማሪ ለእንግዶች ማረፊያ የሚሆኑ ደረጃቸውን የጠበቁ ስድስት ክፍሎች ያሉት ባለ ሁለት ወለል ህንጻ መገንባቱን ስራ እስኪያጁ መናገራቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መረጃ አመላክቷል፡፡