የአፍጢር ሥነ ሥርዓት በተካሄደበት የመሥቀል አደባባይ ጽዳት ተካሄደ

ሚያዝያ 22/2014 (ዋልታ) በሙስሊም ማኅበረሰብ ትልቁ የአፍጢር ሥነ ሥርዓት በተካሄደበት የመሥቀል አደባባይ ጽዳት መርኃ ግብር ተካሄደ።

በጽዳት መርኃ ግብሩ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ የጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አሸቱ ለማ (ዶ/ር)፣ ወጣቶችና ስፖርት  ቢሮ ኃላፊ አብርሃም ታደሰ እና ሌሎች የክፍለ ከተማው አመራሮች እንዲሁም ከቂርቆስ ክፍለ ከተማና ከሌሎችም ክፍለ ከተሞች የመጡ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል፡፡

አዲስ አበባ የመቻቻልና የኅብረ ብሔራዊነት ከተማ እንደመሆኗ ትናንት በእስልምና እምነት ተከታዮች ታላቅ የአፍጢር ሥነሥርዓት የተካሄደ ሲሆን በዚህም አደባባዩን በማጽዳትና ለሌሎች አገልግሎቶች ንጹህ ለማድረግ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በከተማዋ ሙስሊምና ክርስቲያን ወንድማማቾች በፍቅር፣ አንድነትና መቻቻል የሚኖሩባት ከተማ ስለሆነች እንድነታችንን ለማሳየትና ለወገኖቻችን አብሮነታችንን ለመግለጽ ጭምር የጽዳት ፕሮግራሙ  የተዘጋጀ ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ የጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት  ቢሮ ኃላፊ አብርሃም ታደሰ በበኩላቸው ወጣቶች ከስሜታዊነት በመውጣት አንድነትን የሚያጎሉ ጉዳዮችን ለማጠናከር መትጋት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

የከተማ አስተዳደሩ የጽዳት አምባሳደር ሼክ ሃጂ ሸምሱ አባስ በሃይማኖት እና ዘር ቀለም ሳንለያይ አባቶቻችን ያቆዩልንን የመቻቻል ባህል በማጎልበት የአካባቢያችንን ቆሻሻ እንደምንፀየፈው ሁሉ የእኩይ አስተሳሰብንም ከአዕምሯችን ልናጸዳ ይገባል ማለታቸውን ከከንቲባ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።

ለፈጣን መረጃዎች፦

ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW

ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth

ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured

ቲዊተር https://twitter.com/walta_info

አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!