የኢሬቻ ባዛርና ዐውደ ርዕይ በመዲናዋ ተከፈተ

መስከረም 18/2015 (ዋልታ) ለአራት ቀናት የሚቆይ የኢሬቻ ባዛርና ዐውደ ርዕይ በአዲስ አበባ ከተማ ተከፈተ፡፡

በመጪው ቅዳሜና እሁድ የሚከበረውን የኢሬቻ በዓል ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀውን ባዛርና ዐውደ ርዕይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከፍተዋል።

ከንቲባ አዳነች በዚሁ ወቅት አዲስ አበባ ከተማ የኅብረ ብሔራዊነት እና የወንድማማችነት ምልክት መሆኗን ተናግረዋል፡፡

በዚህም የመዲናዋ ነዋሪዎች ሃይማኖታዊና ሕዝባዊ በዓላትን በጋራ በማክበር አንድነታቸውን ይበልጥ እያጠናከሩ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

ኢሬቻ የሰላም፣ የወንድማማችነትና የምስጋና በዓል መሆኑን የተናገሩት ከንቲባዋ አዳነች በዓሉን ወንድማማችነትንና አንድነትን መሰረት ባደረገ መልኩ በጋራ ልናከብረው ይገባል ነው ያሉት፡፡

የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር ዓባይ በበኩላቸው  ኢትዮጵያ ያላት ብዝኃ ባህልና እሴቶች የአብሮነታችን መገለጫዎች ናቸው ብለዋል።

እነዚህን ሃብቶቻችንን ጠብቀን ለመጪው ትውልድ የማስተላለፍ ኃላፊነት አለብን ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡