የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ የአፍሪካ ስመጥር ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች ሽልማትን አሸነፉ

ሐምሌ 23/2014 (ዋልታ) የኢትዮ ቴሌኮም ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ በቴሌኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ የ2022 የአፍሪካ ስመጥር ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች ሽልማትን አሸነፉ።
ዘ ቢዝነስ ኤክዚኪዩቲቭ የተሰኘ በጋና የሚገኝ የፓን ዌስት አፍሪካ ሚዲያ በሞሪሽየስ ባዘጋጀው የ2022 የአፍሪካ ስመጥር ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች ሽልማት ሥነ-ሥርዓት ላይ በአፍሪካ በተለያዩ የንግድ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚዎችን አወዳድሯል።
ለ17ቱ የተባበሩት መንግሥታት ዘላቂ የልማት ግቦች (UN-Sustainable Development Goals) በአፍሪካ ለሚኖረው ስኬት ላደረጉት አስተዋጽኦ በየዘርፋቸው አወዳድሮ ነው የሸለመው፡፡
በቴሌኮሙዩዩኒኬሽን ዘርፍ የሞሮኮው፣ ማሮክ ቴሌኮም፣ የኬንያው ሳፋሪኮም፣ የግብፁ ኢትሳላት እንዲሁም የኢትዮጵያው ኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች ዕጩ ተወዳዳሪ ሆነው ቀርበዋል።
በዚህም የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ የ2022 የአፍሪካ ስመጥር ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች ሽልማት ተሸላሚ መሆናቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ኢትዮ ቴሌኮም ይህንን በማስመልከት ባወጣው መግለጫ “በሽልማቱ የኩባንያችንም የሀገራችንም ኩራት መሆናቸውን አስመስክረዋል” ብሏል።
በዕለቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በሥራ መደራረብ በሞሪሽየስ በአካል መገኘት ባለመቻላቸው በኩባንያው ከፍተኛ ኃላፊዎች ተወክለው ሽልማቱ ተበርክቶላቸዋል ነው የተባለው፡፡