የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አ.ማ በባቡር ደህንነት ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተወያየ ነው

የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት

መስከረም 27/2014 (ዋልታ) የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አ.ማ በባቡር ደህንነት ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት በማድረግ ላይ ነው።

የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት ጄነራል ዳይሬክተር ጥላሁን ሳርካ እንደተናገሩት በባቡር ላይ የሚደርሱ አደጋዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው።

የባቡር ሀዲዲና ቡለን ስርቆት፣ የባቡር እገታና የኤሌክትሪክ ተሸካሚ ሽቦዎችን መቁረጥ በባቡሩ ህልውና ላይ ስጋት ደቅኗል ነው ያሉት። በዚህም አዳማ-ሞጆ-ቢሾፍቱ መስመሮች ላይ ችግሩ እየተባባሰ ነው ተብሏል።

ሽንኔ አካባቢ የባቡር ዕገታ የሚስተዋልበት ሲሆን፣ ገላን አካባቢ የስርቆት ወንጀል ይበዛልም ነው የተባለው።

በ1 ቀን ብቻ 2ሺሕ 789 የባቡር ቡለኖች እና 34 ያህል የሃዲዲ መገጣጠሚያ ብረቶች መሰረቃቸውም ተጠቁሟል።

የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት የደህንነት ክፍል  ኃላፊ ጥበቡ ተረፈ በበኩላቸው፣

ወንጀለኞች ላይ የሚወሰደው እርምጃ አናሳ መሆኑ ስርቆቱን አባብሶታል ብለዋል።

ባቡር ያልገጫቸውን እንስሳቶች ወደ ባቡሩ በማስገባት ካሳ የሚጠይቁ እንዳሉና ግንዛቤ ፈጠራ ላይ  ሰፊ ስራ መሰራት እንዳለበትም ተናግረዋል።

የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት 763 ኪ.ሜ ይሸፍናል።

በተስፋዬ አባተ