የኢትዮጵያ ልማት ባንክ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን ለመደገፍ 8 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር መደበ

መጋቢት 13/2013 (ዋልታ) – የኢትዮጵያ ልማት ባንክ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን ለመደገፍ 8 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር መመደቡን አስታወቀ።
የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች በአምስት የተለያዩ የስልጠና ማእከላት ከ2 ሺህ 500 በላይ ሰልጣኞች የሚሳተፉበት የመጀመሪያ ዙር ስልጠና ተጀምሯል።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዮሐንስ አያሌው በመርሃ-ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር ባንኩ በ2013 በጀት ዓመት 8 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በመመደብ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች በዕውቀት ላይ የተመሠረቱና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የተመደበው ገንዘብ ወጣቶችን ስራ ፈጣሪ በሚያደርግ መልኩ ለማሽነሪ ግዥ ፕሮጀክቶች እና ለሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች እንደሚውልም ነው የጠቆሙት።
ሀገር አቀፍ ስልጠናው ኢንተርፕራይዞቹ ከዚህ በፊት የነበረባቸውን ችግር ፈተው በተሻለ የቢዝነስ አመራር ክህሎት ስራቸውን እንዲያከናውኑ እንደሚያግዝም ገልጸዋል።
ኢንተርፕራይዞቹ ከባንኩ ጋር በቀጣይነት በጋራ ለመስራት ስልጠናውን በአግባቡ ተከታትለው ማጠናቀቅ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በበይነ-መረብ ባስተላለፉት መልእክት ባለፈው ስርዓት ኢኮኖሚው በውስን አካላት ቁጥጥርና ቅብብሎሽ ስር መቆቱን አስታውሰዋል።
ይህም አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ለሀገር ኢኮኖሚ የሚጠበቅባቸውን ያህል አበርክቶ እንዳይኖራቸው አድርጓል ብለዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያ ልማት ባንክ፤ ኢንተርፕራይዞችን ተወዳዳሪና ብቁ ለማድረግ እያከናወነ ያለውን ስራ አድንቀዋል።
ባንኩ ኢንተርፕራይዞችን ለሀገራዊ ለውጥ ብቁ ለማድረግ እያከናወነ ያለው ጥረት ለሌሎች ተቋማት ጥሩ ተሞክሮ እንደሆነ የተናገሩት ደግሞ የሱማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሙስጠፌ መሐመድ ናቸው።
ሀገር አቀፍ ሥልጠናው በዋናነት በቢዝነስ ፕላን አዘገጃጀትና ራዕይ ቀረጻ፣ የንግድ ሥራ አመራር፣ በፋይናንስና ሒሳብ አስተዳደር እንዲሁም በሰው ሀብት አስተዳደር ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።
እንደ ኢዜአ ዘገባ የአዲስ አበባ፣ ባህርዳር፣ ደሴ፣ ጅማና ጅግጅጋ ከተሞች ደግሞ የመጀመሪያ ዙር ስልጠና እየተሰጠባቸው ያሉ ማእከላት ናቸው።
ሁለተኛው ዙር ስልጠና ደግሞ በአዳማ፣ በወላይታ ሶዶ እና በቡታጅራ ከተሞች እንደሚቀጥል ተገልጿል።