የኢትዮጵያ መንግሥት እና የዓለም ምግብ ፕሮግራም በትግራይ ክልል በጋራ ሰብአዊ እርዳታ ለማድረስ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
ስምምነቱ የመጣው የሰላም ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ከተመድ የዓለም ምግብ ድርጅት ሥራ አስፈጻሚ ዴቪስ ቤስሊ (ዶ/ር) ጋር በትግራይ ክልል እየተካሄደ ያለው የሰብአዊ ድጋፍ ሁኔታ በጋራ የመስክ ጉብኝት ማደረጋቸውን ተከትሎ ነው።
በትግራይ ክልል የተካሄደውን ሕግ የማስከበር ዘመቻ ተከትሎ ሁለንተናዊ ድጋፍ ለማድረግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የደኅንነት እና ፀጥታ ምክትል ዋና ፀሐፊ፣ ከስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር እና ከዓለም ምግብ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ጨምሮ ሌሎች የተመድ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር በመምከር በጋራ ለመሥራት የሚያስችል ቅርርብ መፈጠሩም ተመልክቷል።
በዚሁ መሠረት የኢትዮጵያ መንግሥት እና የዓለም ምግብ ፕሮግራም በትግራይ ክልል የሰብዓዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ድጋፉ በስፋት እና በተፋጠነ መልኩ እንዲከናወን መስማማታቸው የዓለም ምግብ ፕሮግራም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
በተመሳሳይ በመስክ በተካሄደ ምልከታ መቀሌ የሚገኘው የእህል ማከማቻ ለቀጣይ ሁለት ወራት 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ዜጎችን መመገብ የሚያስችል የምግብ ክምችት መኖሩን ባለሥልጣናቱ ማረጋገጣቸውን የሰላም ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
በክልሉ የእርዳታ ስርጭት ተደራሽነትን ለማስፋት በ36 ወረዳዎች 92 የምግብ ማሰራጫ ማእከላት እንደተከፈቱ እና ከ92 ማእከላት አራቱ ስደተኞች ያሉባቸውን ቦታዎች የሚሸፍኑ እንደሆነም ታውቋል።
እስካሁን ባለው እንቅስቃሴ በክልሉ የሚገኙ ሰብአዊ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎችን ተደራሽ ማድረግ እንደተቻለ እና የመንግሥት ድርሻ 70 ከመቶ መሆኑን ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ገልጸዋል።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ቤስሊ በበኩላቸው የሰብአዊ ድጋፍ ለሚመለከታቸው ዜጎች እየደረሰ እንደሆነ መመልከታቸውን ገልጸው፣ በቀጣይ ለሚከናወኑ ድጋፎች ድርጅታቸው አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም በመጪው የካቲት ወር 300 ሺህ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ለተረጂዎች እንዲደርስ ለማድረግ ለኢትዮጵያ መንግሥት ድጋፍ እንደሚሰጥ በመግለጫው አስታውቋል።