የኢትዮጵያ መንግስት ሰላም ለማምጣት ብዙ ርቀት ተጉዟል ሲሉ አቶ ዛዲግ አብርሃ ገለጹ

ታኅሣሥ 7/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ መንግስት ወደ ጦርነት ላለመግባትና ጦርነቱ ከተጀመረም በኋላ ወደ ሰላም ለመምጣት ብዙ ርቀት መጓዙን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሚኒስትር ዛዲግ አብርሃ ገልጸዋል፡፡
ሚኒስትሩ ከዶቼ ቬሌ “ኮንፍሊክት ዞን” ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት አሸባሪው ሕወሓት ያላከበረውን የተኩስ አቁም የኢትዮጵያ መንግስት በተናጠል ማድረጉ ለሰላም የሄደውን ርቀት የሚያሳይ ነው፡፡
አሸባሪው ቡድን ስምምነቱን ባለማክበሩ እና ባለመፈለጉ በሕዝብ ከፍተኛ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጥፋት እንዲደርስበት ማድረጉን አንስተዋል፡፡
በአማራ እና አፋር ክልሎች ወረራ የፈጸመው አሸባሪው የሕወሓት ቡድን የንጹሃንን ህይወት ከማጥፋቱም በተጨማሪ ሴቶች መድፈሩን እና ንብረት መዝረፉን እንዲሁም ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የተለያዩ ከተሞች ላይ ውድመት ማድረሱን አስረድተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የሰብኣዊ መብት ምክር ቤት በጠራው ስብሰባ ላይ ለምን እንደማትካፈል የተጠየቁት ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በስብሰባው የማትካፈለው ብቸኛ አገር አለመሆኗን በመጥቀስ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
አክለውም አንድም አፍሪካዊ አገር በስብሰባው እንደማይካፈል እና ይህም አሸባሪው ሕወሓት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ያደረሰውን የሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት መረዳታቸውን የሚያመላክት እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡