የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ባለስልጣን ሰራተኞች ለሰራዊቱ ደም ለገሱ

ነሃሴ 5/2013 (ዋልታ) –የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ባለስልጣን ሰራተኞች ለመከላከያ ሰራዊት ደም ለግሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እድሪስ የሀገርን ህልውና ለማፍረስ የተነሳውን አሸባሪ የጥፋት ኃይል ህዝቡ ከመከላከያ ሰራዊቱ፣ ከክልል ልዩ ኃይሎች እንዲሁም ከሚልሻዎች ጎን በመቆም ደም በመለገስ የሀገር ግዴታውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡

አክለውም የህወሓት ቡድን ከሚያደርሰው ጥፋት በተጨማሪ ሀሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨት እውነትን በሀሰት በመቀየር በማህበረሰቡ ላይ የተሳሳተ መረጃ እያሠራጨ በመሆኑ ከመንግስት የሚወጡትን ትክክለኛ መረጃዎች  በመጠቀም የጥፋት ኃይሉን የሃሰት ወሬ ማውገዝ ይገባል ብለዋል፡፡

አሸባሪውን ለመመከት ከደም ልገሳ በተጨማሪ ማህበረሰቡ በተቻለው አቅም ለፀጥታ ኃይሉ አስፈላጊውን ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዮናታን ተስፋየ በበኩላቸው   የመከላከያ ሰራዊቱ፣ የክልል ልዩ ኃይሎች እንዲሁም ሚልሻዎች  ከዛም አልፎ ወጣቱ ትውልድ  የሀገሩን ክብር ለመጠበቅ፣ የውጭ ወራሪዎችን ምኞት ለመግታትና ሀገርን ለማፈራረስ የሚመኙትን የሀገር ውስጥ ጠላቶች ለመመከት መተኪያ የሌላትን ሕይወቱን ለመስጠት በግንባር ለተሰለፈው  የፀጥታ ኃይል ደም መለገሳችን ሀገራዊ ግዴታችን ነው ብለዋል፡፡

(በአመለወርቅ መኳንንት)