ግንቦት 25/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያን ገጽታ ለዓለም ለማስተዋወቅ ያለመ ‘የኢትዮጵያ ስጦታዎች’ ዓለም ዐቀፍ ፌስቲቫል ተጀመረ።
ፌስቲቫሉ ከአንድ ወር በኋላ በሰሜን አሜሪካ፣ እስያ፣ አውሮፓና በመካከለኛው ምስራቅ በሚገኙ አገራት እንደሚዞር ተገልጿል።
‘የኢትዮጵያ ስጦታዎች’ ዓለም ዐቀፍ ፌስቲቫል ማስጀመሪያ መርኃ ግብር ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ዓለም ዐቀፍ የማኅበረሰብ ክፍሎችና ታዋቂ ግለሰቦች በተገኙበት በወዳጅነት አደባባይ እየተካሄደ ነው።
ዝግጅቱ የኢትዮጵያን ትክክለኛ ገጽታ ለዓለም በማስተዋወቅና የተዛቡ ትርክቶችን በማረም የቱሪዝምና ኢንቨስትመንት ፍሰትን ለመጨመር ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ እንዳሉት ፌስቲቫሉ ኢትዮጵያ ያላትን ባህል በማስተዋወቅ ፋይዳው የጎላና በኢትዮጵያ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ ለመላው ዓለም በማሳየት የገጽታ ግንባታ እንዲሁም ኢንቨስትመንት ለመሳብ ያግዛል።
የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ ምድረ-ቀደምት መሆኗን ተናግረዋል።
ይህንን ሀብት ወደ ኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለመቀየር የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሆነም ገልጸዋል።
በፌስቲቫሉ መክፈቻ ማስጀመሪያ የጥበብ፣ ግብርና፣ ዕደ ጥበብ፣ የቡና አፈላልና ሌሎች ትዕይንቶች ለእይታ ቀርበዋል።
ፌስቲቫሉ ከአንድ ወር በኋላ በጀርመን፣ አሜሪካ፣ ካናዳና በተለያዩ የዓለም አገሮች በመዘዋወር ኢትዮጵያ ያላትን ባህል በማስተዋወቅ የገጽታ ግንባታ እንደሚከናወን ኢዜአ ዘግቧል።