የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ከ3.7 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ተጎጂዎች ድጋፍ ማድረጉን አስታወቀ

ግንቦት 25/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ባለፉት 9 ወራት ከ3 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ተጎጂዎች ሰብዓዊ እርዳታ መስጠቱን አስታውቋል።

ባለፉት 3 ወራት በተከሰቱ ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች ለተጎዱ 20 ሺህ ወገኖች የምግብ እርዳታ፣ እንዲሁም 30 ሺህ ለሚሆኑት ደግሞ ምግብ ነክ ያልሆኑ ሰብዓዊ ድጋፎች ማድረጉን የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የኮሙኒኬሽን ኃላፊ ሰለሞን አሊ (ዶ/ር) ገልጸዋል።

ማህበሩ 15 ሺህ ለሚሆኑ ልዩ ልዩ የመድኃኒት እና ምግብ ነክ እርዳታዎችን ማድረጉንም አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በሀገሪቱ ባሉት ከ180 በላይ ቅርንጫፎች አማካኝነት የህብረተሰቡን ተሳትፎና ድጋፍ በተለያየ መልኩ ለማረጋገጥ እየሰራ እንደሚገኝ ኃላፊው ተናግረዋል።

ማህበሩ በኢትዮ- ቴሌኮም የሞባይል ኤስኤምኤስ መልዕክት መላላኪያ 9400 በመዘርጋት ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማግኘቱንም ነው ዶ/ር ሰለሞን የገለጹት፡፡

ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ አፋር፣ ሶማሌ እና ደቡብ ክልሎች የሰብዓዊ እርዳታ እና ድጋፉ የተዳረሰባቸው ክልሎች መሆናቸውን የኮሙኒኬሽን ኃላፊው ተናግረዋል ሲል የዘገበው ኢብኮ ነው።