የኢትዮጵያ ትልቁ ወዳጇ ውስጣዊ አቅሟ ነው ሲሉ ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ገለጹ

የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ

መስከረም 28/2014 (ዋልታ) የአሸባሪ ቡድኑ ጥቃት ኢትዮጵያዊያን ቀፎው እንደተነካበት ንብ በጋራ እንዲቆሙ አድርጓል ሲሉ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ተናገሩ።

ርዕሰ መስተዳደሩ ይህን ያሉት አቶ ምህረተአብ ሙሉጌታ የተባሉ ባለሀብት በአፋር ክልል ችግር ለደረሰባቸው ዜጎች እንዲውል ያደረጉትን የግማሽ ሚሊየን ብር ድጋፍ በተረከቡበት መርኃግብር ላይ ነው።

አቶ ምህረተአብ ድጋፉን ያደረጉት ኢትዮጵያ ያጋጠማትን የውስጥና የውጭ ፈተናዎች ለመቋቋም ለሚታገሉ የአፋር ልዩ ኀይልና ከመኖሪያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ያላቸውን ክብር ለማሳየት መሆኑን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደረው የአፋር ሕዝብ አሸባሪው የህወሓት ቡድን የጅቡቲን መስመር ለመዝጋት ያደረገውን እንቅስቃሴ ከመከላከያ ሠራዊቱ ጋር ባደረገው ተጋድሎ ቡድኑን ከስፍራው ማስወጣቱን አድንቀዋል።

“ለተፈናቀሉ ወገኖቼ ድጋፉን የማደርገው በኢትዮጵያዊነት መተባበር የገጠመንን ፈተና ለመወጣት ነው” ብለዋል። ይህን የፈተና ጊዜ ተጋግዘን ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ መውሰድ ይገባናልም ነው ያሉት።

በቀጣይም በሌሎች ክልሎች ለሚገኙ ተፈናቃዮች አቅማቸው በፈቀደ መጠን ድጋፉን እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

ባለሃብቱ ቀደም ሲልም በጥሬ ገንዘብና በቁሳቁስ 2 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር የሚገመት ድጋፍ ለመከላከያ ሠራዊት ማድረጋቸው ተወስቷል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ለተደረገው ድጋፍ አመስግነው፣ ወጣቱ ባለሃብት በአዲስ መንግስት ምስረታ ማግስት ለክልሉ ሕዝብ በማሰብ የዜግነት ግዴታውን በመወጣቱ አድንቀዋል።

ግለሰቦችና ተቋማት ለችግር የተጋለጡ የአፋር ወገኖችን ለመርዳት እያደረጉት ላለው ድጋፍም አመስግነዋል።

“የኢትዮጵያ ትልቁ ወዳጇ ውስጣዊ አቅሟ ነው” ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ “ትልቁ ጠላቷ ደግሞ ድክመቷ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

አሸባሪው ቡድን አገር የመምራት ዕድል አግኝቶ እንኳን ራሱን ነፃ አውጪ አድርጎ እንደሚጠራ ያስታወሱት አቶ አወል፣ ቡድኑ የኢትዮጵያ ጠላት መሆኑን ሁሉም ዜጋ መረዳት አለበት ብለዋል።

ለትግራይ ክልል ሕዝብ ያልሆነ ኃይል ለሌላውም እንደማይበጅ ገልፀው፣ ሕዝቡን ለረሃብ መዳረጉን፣ ትግራይን ማፍረሱን፣ ታዳጊዎችንም ለጦርነት እየማገደ መሆኑን አንስተዋል።

ቡድኑ ወጣቶችን እየጨረሰ የ’አሸንፈናል’ የሀሰት ፕሮፓጋንዳ እየነዛ ቢሆንም ሲያልመው ከነበረው አፋር ምድር እንዲወጣ መደረጉን ገልፀዋል።

የአፋር ህዝብ በአገሩ አንድነትና ሕልውና እንደማይደራደር ገልፀው፤ ቡድኑ አፋርን ተጠቅሞ ኢትዮጵያን ለማፍረስ አልሞ እንደነበር፤ በሕዝቡና በመከላከያ ሠራዊቱ ሕልሙ በአጭር መቀጨቱን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የአሸባሪ ቡድኑ ጥቃት ኢትዮጵያዊያን ቀፎው እንደተነካበት ንብ በጋራ እንዲቆሙ አድርጓል ያሉት አቶ አወል የሽብር ኃይሉ እንዲደመሰስ ጥረታችን ይቀጥላል፤ አንዘናጋም ብለዋል።