የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ከ2 ዓመታት በኋላ ወደ ናይጄሪያ ኢኑጉ ከተማ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ

መስከረም 10/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሁለት ዓመታት በኋላ ወደ ናይጄሪያ ኢኑጉ ከተማ የድጋሚ በረራ አገልግሎት ሊጀምር መሆኑን በኢትዮጵያ አየር መንገድ ናይጄሪያ ቢሮ ኃላፊ ሽመልስ አራጌ አስታውቋል፡፡

አየር መንገዱ የድጋሚ በረራውን ከመስከረም 21 ቀን ጀምሮ ሲጀምር ቦይንግ 787 አውሮላንን እንደሚጠቀም ተገልጿል፡፡

ወደ ከተማዋ የሚደረገው በረራ በሳምንት ሶስት ቀናት ማለትም ዘውትር ረቡዕ፣ አርብ እና ቅዳሜ መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

መስከረም 21 ቀን ናይጄሪያ ከቅኝ ግዛት ነጻ የወጣችበት ቀን መሆኑን አስታውሰው፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ናይጄሪያ መብረር ከጀመረበት እ.ኤ.አ ከ1960 ጀምሮ በኢትዮጵያ እና በናይጄሪያ መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከሩን ተናግረዋል፡፡

በዚህ የነጻነት ቀን ወደ ኢኑጉ ከተማ በረራ መጀመር ደግሞ አሁንም በኢትዮጵያ እና በናይጄሪያ መካከል የነበረውን የቆየ የሁለትዮሽ ግንኙነት የበለጠ ያጠናክረዋል ብለዋል፡፡

ኃላፊው አክለውም አየር መንገዱ ወደ ኢኑጉ ከተማ ሲያደርግ የነበረውን በረራ እ.ኤ.አ በ2019 ያቋረጠው የናይጄሪያ የበረራ ባለስልጣን አየር መንገዱን ለጥገና መዝጋቱን ተከትሎ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ኢዜአ እንደዘገበው የኢኑጉ ከተማ አየር መንገድ ለጥገና ከመዘጋቱ በፊት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ከተማዋ ዓለም አቀፍ በረራ የሚያደርግ ብቸኛው አየር መንገድ እንደነበር ያስታወሱት ኃላፊው፣ አሁን ላይ አስፈላጊው ጥገና ተደርጎለት ለአገልግሎት ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ይህንን ተከትሎ አየር መንገዱ እ.ኤ.አ በ2020 የሀገር ውስጥ በረራ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ እንዲሁም እ.ኤ.አ ነሃሴ 2021 የዓለም አቀፍ በረራ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ተክትሎ ነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ከተማዋ ለመብረር የተዘጋጀው ብለዋል፡፡