የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ከልማት አጋሮች ጋር ውይይት አካሄደ

ሰኔ 24/2014 (ዋልታ) የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ለኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን በሚደረገው ድጋፍ ላይ ከልማት አጋሮችን ጋር ምክክር አካሄደ፡፡

የአገራዊ የምክክር ኮሚሽን ሰብሳቢ መስፍን አርአያ (ፕ/ር) ኮሚሽኑ እስካሁን የሰራቸውን ተግባራትና በቀጣይ ስለሚያከናውናቸው ተግባራት ላይ ለልማት አጋሮች ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ የተለያዩ የፖለቲካ፣ የአመለካከት ፣ የሃሳብ ልዩነቶች ብሎም አለመገባባቶች በሰፊ የሕዝብ ውይይቶች ሊፈቱ እንደሚገባ መንግሥት በጽኑ ያምናል ሲሉ ገልፀዋል፡፡

ሚኒስቴር ዴኤታዋ እንደገለፁት ሁሉንም ያሳተፈ ሀገራዊ ውይይት ማካሄድ በሀገሪቱ ላይ የተደቀኑ ፈተናዎችን ለመቋቋም እንደሚያስችል ተናግረው ሥራውን የተቀናጀና ተቋማዊ ማድረግን ይጠይቃል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም ለኮሚሽኑ የሚደረጉ የልማት ድጋፎችን የትረስት ፈንድ በማቋቋም እንዲያስተባብር ውክልናም ሰጥቷል።

ፕሮግራሙ በቀጣይ ለኮሚሽኑ በሀብት አሰባሰብና በፈንድ አስተዳደር ዙሪያ ድጋፍ ያደርጋል መባሉን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡