የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ የእንኳን አደረሳቹህ መልዕክት አስተላለፉ

ታኅሣሥ 28/2015 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ የእንኳን አደረሳቹህ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ፓትርያሪኩ ብፁዕ አቡነ ማቲያስ በመልዕክታቸው በዕለተ ልደቱ ስለሰላም እንዲዘመር ላደረገ ፈጣሪ ምስጋና ይገባዋል ብለዋል፡፡

የፍቅርና የርህራሄ አምላክ የሆነው ፈጣሪ ለሰው ልጆች የሚሰጠውን ዘላቂና ፍፁም ሰላም በመሲዉ ኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት አሳይቶናል ብለዋል።

ክርስቶስ የሰላም አለቃ መሆኑን አሳይቷል ያሉት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ እርቀ ሰላም የማይፈታው ችግር እንደሌለ ጠቁመዋል።

በሀገሪቱ ተከስቶ የነበረው ችግር ረግቦ ሰላም መፈጠሩ የእግዚአብሔር ስጦታ በመሆኑ ልንጠብቀው ይገባል ነው ያሉት።

በመጨረሻም ብፁዕነታቸው የእንኳን አደረሳቹህ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

እንዲሁም የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች ዐቢያተ ክርስቲያናት ካውንስል ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል፡፡

የካውንስሉ ጠቅላይ ጸሐፊ ቄስ ደረጀ ጀንበሩ ያልታረቀ ማስታረቅ ስለማይቻለው በቅድሚያ እኛ ራሳችን ታርቀን የሰው ልጆች በሙሉ ከአምላካቸው፣ ከራሳቸውና ከእርስ በርሳቸው ጋር ይታረቁ ዘንድ ጊዜያችንን በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባናል ብለዋል።

ለእኛ ለኢትዮጵያዊያን ከማንኛውም ነገር በፊት ቅድሚያ ልንሰጠው የሚገባን ብርቱ ተግባር ቢኖር እርቅና ሰላም ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

በሱራፌል መንግስቴ እና በብርቱካን መልካሙ