የኢትዮጵያ ወጣቶች ኦሎምፒክ በተለያዩ ውድድሮች መካሄዱን ቀጥሏል

ግንቦት 24/2014 (ዋልታ) በሀዋሳ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ወጣቶች ኦሎምፒክ የተለያዩ ውድድሮች ተካሂደው አሸናፊዎች ተለይተዋል፡፡

በውድድሩ የ4ኛ ቀን ውሎ የአትሌቲክስ ቦክስ፣ የእግር ኳስ እና ጠረጼዛ ቴኒስ የማጣሪያ ውድድሮች ሲካሄድ የክብደት ማንሳት፣ የብስክሌት እና የስሉስ ዝላይ ውድድሮች ደግሞ የፍፃሜ ጨዋታዋች ተከናውነዋል።

በሜዳ ላይ ተግባራት ስሉስ ዝላይ በተደረገ ውድድር ከደቡብ ክልሉ ዮሴ ኦባንግ 15:41 በመዝለል የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ሆኗል።

ኡመድ ኡጅሉ ከጋምቤላ በ15:09 ሁለተኛ በመሆን የብር ሜዳሊያ ሲያገኝ የአዲሰ አበባ ከተማ አስተዳደሩ ኡመዱ ኦባሳ በ15:08 በመዝለል ነሀሰ አግኝቷል።

ዛሬ በተደረጉ የአትሌቲክስ ውድድሮች በ100 ሜትር እና በ800 ሜትር  በሁለቱም ፆታ የማጣሪያ ውድድሮች ተደርገዋል።

በሴቶች ክብደት ማንሳት የፍፃሜ ውድድር የ49 ኪሎግራም ካታጎሪ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ወርቅ ሜዳሊያ ሲያገኝ ኦሮሚያ ብር አድስ አበባ ደግሞ ነሀስ አግኝተዋል።

በብስክሌት የቡድን ክሮኖ ሜትር በሴቶች 20 ኪሎ ሜትር እና በወንዶች 30 ኪሎ ሜትር አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሁለቱም ፆታ የወርቅ ሜዳሊያ ማስመዝገብ ችሏል።

በአጠቃላይ ውድድር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 6 የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማግኘት ውድድሩን እየመራ ይገኛል።

የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ወጣቶች ኦሎምፒክ ጨዋታ “ትክክለኛ እድሜ ለኢትዮጵያ ስፓርት እድገት” በሚል መሪ ሃሳብ ከግንቦት 21 እስከ ሰኔ 4 በሀዋሳ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

መሰረት ተስፋዬ (ከሀዋሳ)