የኢትዮጵያ የምግብ መዋቅራዊ ለውጥ የ10 ዓመት እቅድ በነገው እለት ይፋ ይደርጋል

ሐምሌ 07/2013 (ዋልታ) – የኢትዮጵያ የምግብ መዋቅራዊ ለውጥ የ10 ዓመት እቅድም በነገው እለት ይፋ እንደሚደረግ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

የ10 ዓመት የኢትዮጵያ የምግብ ሥርዓት መዋቅራዊ ለውጥን የተመለከተ ጉባኤ ነገ እንደሚያካሂድ ያስታወቀው ኢንስቲትዩቱ፣ በጉባኤው የኢትዮጵያ የምግብ መዋቅራዊ ለውጥ የ10 ዓመት እቅድም ይፋ ይደርጋል ብሏል።

የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይይሬክተር ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ መዋቅራዊ ለውጡ አሁን ያለውን የአመጋገብ ሥርዓት ማሻሻል፣ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ ምርት እና ምርታማነት እንዲሁም የምግብ አቅርቦትን ማሻሻል የሚሉ ግቦችን ይዟል ብለዋል።

በጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ አማካሪ ዶክተር ፍሬው ለማ በበኩላቸው፣ በኢትዮጵያ የተሰባጠረ ምግብ የሚያገኙ ህፃናት ቁጥር 12 በመቶ ብቻ መሆናቸውን ገልጸው፣ 2 ነጥብ 6 በመቶ ያህሉ ዜጎች ብቻ አትክልትና ፍራፍሬ እንደሚመገቡ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ያለው የአመጋገብ ሥርዓት ባለመቀየሩ በዘጠኝ ዓመታት ውስጥ ከአመጋገብ ሥርዓት ጋር በተያያዘ የሚከሰት የሞት መጠን በ18 በመቶ መጨመሩንም አንስተዋል።

ሚኒስትሮች፣ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በሚገኙበት ጉባኤ ላይ ይፋ የሚደረገው የ10 ዓመት የምግብ ሥርዓት መዋቅራዊ ለውጥም ለችግሩ መፍትሄን የያዘ ነው ተብሏል።

የኢትዮጵያ የምግብ ሥርዓት መዋቅራዊ ለውጥ በቀጣይ 10 ዓመታት ለእያንዳንዱ ዜጋ የሚያስፈልገውን ምግብ ለማድረስ ቃል ኪዳን የሚገባበት መሆኑም ተጥቅሷል።

(በትዕግስት ዘላለም)