ግንቦት 21/2013 (ዋልታ) – ከስድስት አስርት ዓመታት በላይ ያስቆጠረው የኢትዮጵያ የዳኝነት አገልግሎት ክፍያ ደንብ ሊሻሻል ነው።
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዳኝነት ክፍያ ማሻሻያ ረቂቅ ደንብ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጓል።
የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት መአዛ አሸናፊ በውይይቱ ወቅት እንዳሉት የኢትዮጵያ የዳኝነት የክፍያ ማሻሻያ ደንብ ከ68 ዓመት በላይ ያስቆጠረ ነው።
ደንቡ ፍርድ ቤቶች ለሚሰጡት አገልግሎት ተመጣጣኝ ገቢ እንዳያገኙ እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን ጠቅሰዋል።
ክፍያው ወቅቱን ያላገናዘበ በመሆኑ አገልግሎቱን ለማሻሻል፣ መሰረተ ልማቱን ለመገንባትና የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነቱ እንዳያድግ አድርጓልም ብለዋል።
በመሆኑም አሁን የተሻሻለው ረቂቅ ደንብ የህብረተሰቡን የመክፈል አቅምና ወቅታዊ የዋጋ ግሽበት ባገናዘበ መልኩ መሆኑን አስረድተዋል።
የቀደመው የአገልግሎት ክፍያ ደንብ ከፍርድ ቤቶች የመዝገብ ግልባጭ ለመውሰድ ሃምሳ ሳንቲም የሚጠይቅ ሲሆን ይህ ክፍያ በአሁኑ ወቅት ያለውን የአንድ የወረቀት ሂሳብ እንኳን የማይሸፍን መሆኑን ፕሬዝዳንቷ አስረድተዋል።
በፍርድ ቤቶች እየመጡ ያሉ ጉዳዮች ውስብስብና ሰፊ በመሆናቸው ይህንን መሸፈን የሚያስችል ገቢ ስለሚያስፈልግ የማሻሻያ ረቂቁ መዘጋጀቱን አብራርተዋል።
በየዓመቱ የሚመጡ የፍርድ ቤት ጉዳዮች ከሰባት በመቶ በላይ እያደገ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።
ለመጨረሻ ጊዜ ዛሬ ለውይይት የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ከባለድርሻ አካላት ግብአት ታክሎበት በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚቀርብ ፕሬዝዳንቷ ተናግረዋል።
የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ በዓለም አቀፍ ተሞክሮ የተቃኘና የተሟላ አገልግሎት የሚሰጥ ነው ብለዋል።
ፍርድ ቤቱ ካለፉት ሶስት ዓመታት ጀምሮ በርካታ የለውጥ ስራዎችን እያከናወነ ሲሆን የዳኝነት አገልግሎት ክፍያ ደንብ የዚህ አንዱ አካል መሆኑን ጠቁመዋል።
እንደ ኢዜአ ዘገባ አዲሱ ረቂቅ ደንብ በአገልግሎቶች ተመጣጣኝ የዳኝነት ክፍያን እንዲኖር፣ የዳኝነት ክፍያን ፍርድ ቤቶች እንዲያስተዳድሩት፣ ዘመናዊና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲኖር ያስችላል ተብሏል።