መጋቢት 17/2013 (ዋልታ) – የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት በነገው እለት የጥራት መስፈርትን ላሟሉ ተቋማት ሽልማትን እንደምሰጥ አስታውቋል::
ድርጅቱ ከኢፌዴሪ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ጋር በጋራ በመሆን በጤናማ የውድድር መንፈስ ውጤታማ በመሆን ለጥራት የሚተጋ ተቋም የመፍጠር እስቤን ይዞ ተቋማትን ሲያወዳድር መቆየቱን ገልጿል::
የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ውድድሩ አለም አቀፍ የልህቀት ሞዴልን መሰረት በማድረግ የኢትዮዽያ ጥራት ሽልማት ድርጅት ባዘጋጀው የማወዳደሪያ መስፈርት የተገመገመ መሆኑም ተመላክቷል::
የሀብት ስራ አመራር፣ የስራ ሂደት አመራር፣ የደንበኞች የእርካታ መጠን፣ አቅጣጫዎች እና ስልቶች የአገልግሎት አሰጣጥ አፈፃፀም እንዲሁም ማህበራዊ ተሳትፎ ከብዙ በጥቂቱ ለብቁ ተቋም መወዳደሪያ መስፈርቶች መሆናቸውም ተጠቁሟል::
በነገው እለት በሚካሄደው የጥራት ሽልማት አንድ ተቋም የከፍተኛ አድናቆት የምስክር ወረቀት ተሸላሚ፣ ሰባት ተቋማት የአድናቆት የምስክር ወረቀት ተሸላሚ፣ አንድ ተቋም የተሳትፎ የምስክር ወረቀት እንደሚያገኝ እንዲሁም አንድ ተቋም ከደረጃ በታች አፈፃፀም ማስመዝገቡን የኢትዮዽያ ጥራት ሽልማት ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ቴድሮስ መብራቱ አስታውቀዋል::
(በሄብሮን ዋልታው)