የኢትዮጵያን ሕዝብ ደጀኑ ያደረገ ሠራዊት የሚያሸንፈው ሃይል አይኖርም- ኮሎኔል ጌትነት አዳነ

ኮሎኔል ጌትነት አዳነ

ሐምሌ 14/2013 (ዋልታ) – “የኢትዮጵያን ሕዝብ ደጀኑ ያደረገ ሠራዊት የሚያሸንፈው ሃይል አይኖርም” ሲሉ የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ ገለጹ።

የአገር መከላከያ ሰራዊቱ ለህዝብ ወገንተኛ የሆነ የሞራል ባለቤት መሆኑን ገልጸው፣ ሠራዊቱ መቐሌን ለቆ የወጣው አቅመ ደካሞችና ንጹሃን ላይ ጉዳት እንዳይደርስ መሆኑን ተናግረዋል።

“ክብር ለመከላከያ ሠራዊታችን” በሚል የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና ሌሎች አካላት የተገኙበት ውይይት ተካሂዷል።

በውይይቱ አሸባሪው ህወሓት በአገር መከላከያ ሠራዊት እንዴት እንደተሸነፈ፣ በምን መልኩ ወደ ትንኮሳ እንደተመለሰና በቀጣይ ከሕዝቡ ምን ይጠበቃል በሚሉ ጉዳዮች ገለጻ ተደርጓል።

ሠራዊቱ ግዳጁን በአግባቡ ተወጥቶ ከመቀሌ መውጣቱም ተገቢ እንደነበረ ተገልጿል።

እንደ ኮሎኔል ጌትነት ገለጻ፤ ኢትዮጵያ በታሪኳ የተቃጡባትን ጥቃቶች ስትመክት የኖረችው ሁሌም ፍትሃዊ ጦርነት ስለምትገጥም ነው።

የሕዝቦቿ አንድ ሆኖ የመቆም የዳበረ ባህልም የአሸናፊነቱ ምስጢር መገለጫ እንደሆነ አብራርተዋል።

አሸባሪው የህወሓት ቡድን የሠራዊቱን ትዕግስት የሚፈታተኑ ተግባራት ሲፈጽም ቆይቶ በመጨረሻ ክህደቱን በገሃድ ማሳየቱን አስታውሰዋል።

አሁንም ሠራዊቱ መቀሌን ለቆ የወጣው በሠራዊቱ ግዳጅ አፈጻጸም መመሪያ ‘አቅመ ደካሞችን ጠብቅ ተንከባከብ’ በሚለው መርህ መሰረት እንደሆነ ገልጸዋል።

አሸባሪው ህወሃት ነፍሰጡር እናቶችን ጭምር ለጦርነት እያሰለፈ መሆኑን ጠቁመው፣ “ሠራዊቱ በእነዚህ ሰዎች ላይ የመተኮስ ሞራል የለውም” ብለዋል። ሠራዊቱ አሁንም በተጠናከረ ሁኔታ ስራውን እየከወነ መሆኑንም ጠቁመዋል።

አቶ መለሰ አለሙ

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የዴሞክራሲ ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ አቶ መለሰ አለሙ በበኩላቸው፣ የመዲናዋ ነዋሪ ከሠራዊቱ ጎን መሆኑን እያስመሰከረ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

እስካሁንም ነዋሪው ለሠራዊቱ በገንዘብ ብቻ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሰው፣ በቀጣይም ድጋፉን ማጠናከርና የአካባቢውን ሠላም መጠበቅ እንዳለበት አሳስበዋል።

እንደ ኢዜአ ዘገባ የውይይቱ ተሳታፊዎችም አስፈላጊ ከሆነ እስከ ግንባር ድረስ ሄደው ሠራዊቱን ለማገዝ ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል።