የ’ኤች አር 6600’ እና ‘ኤስ 3199’ ረቂቅ ሕጎች የሚቃወሙ ሰላማዊ ሰልፎች በአሜሪካ ከተሞች ይካሄዳሉ

ሚያዝያ 1/2014 (ዋልታ) የ’ኤች አር 6600 እና ‘ኤስ 3199’ ረቂቅ ሕጎች የሚቃወሙ ሰላማዊ ሰልፎች በአሜሪካ ዋሺንግተን ዲሲና ሎስ አንጀለስ ከተሞች ይካሄዳሉ።
ነገ በዋሺንግተን ዲሲ ዋይት ሃውስ ፊት ለፊት እንደሚካሄድ ሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ ማኅበር የዋሺንግተን ዲሲ ግብረ ኃይል ሰብሳቢ ጣሰው መላከህይወት ገልጸዋል።
“ኤች አር 6600 እና ኤስ 3199 ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያንን የሚጎዳ ነው”፣ ”ሕጎቹ የኢትዮጵያና አሜሪካ ግንኙነትን የሚጎዱ ናቸው”፣ ”ማዕቀብ ይገላል” እና “ኤችአር 6600 እና ኤስ 3199 ይሰረዙ” የሚሉ መፈክሮች በሰልፈኞቹ እንደሚተላለፉ አመልክተዋል።
በሰልፉ ላይ ከኢትዮጵያዊያን በተጨማሪ ኤርትራዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች እንደሚሳተፉ ተናግረዋል።
ዳያስፖራው ሕጎቹ በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርሱትን ጉዳት በየአካባቢያቸው ለሚገኙ የኮንግረስ አባላትና ሴናተሮች በማስረዳት እንዳይደግፉት የማድረግ ጥረቱን ማጠናከር እንደሚጠበቅበት አመልክተዋል።
በዳያስፖራው አደረጃጀት በኩል ሕጎቹ ድምጽ እንዳይሰጥባቸው ተሰሚነት ያላቸውን የኮንግረስ አባላትና ሴናተሮች የማነጋጋር ሥራ እየተከናወነ እንደሆነ አስረድተዋል።
መንግሥት ከአሜሪካ መንግሥት ጋር በሚኖረው ግንኙነት ረቂቅ ሕጎቹ እንዳይጸድቁ የሚያደርገው የዲፕሎማሲ ጥረትና በቅርቡ የወሰዳቸው እርምጃዎች የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ወሳኝ እንደሆነም ነው የገለጹት።
ዳያስፖራው በአንድነት በመቆም ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያዊያንን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥሉት ሕጎች እንዳይጸድቁ አስፈላጊውን ጥረት እንዲያደረጉ የግብረ ኃይሉ ሰብሳቢ ጣሰው ጥሪ አቅርበዋል።
በተያያዘ ዜና ‘ኤችአር 6600’ ረቂቅ ሕግን የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ከነገ በስቲያ በካሊፎርኒያ ግዛት ሎስ አንጀለስ ከተማ ይካሄዳል።
በሰልፉ ላይ ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያን እንደሚሳተፉ ኢዜአ ከሰልፉ አስተባባሪዎች ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
ሰልፎቹ በረቂቅ ሕጉና የሕጉ ተባባሪ አርቃቂ በሆኑት የካሊፎርኒያው የኮንግረስ አባል ብራድ ሼርማን ላይ ተቃውሞ እንደሚያሰሙ ተነግሯል።
ትውልደ ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያኑ በጥቅምት ወር 2015 ዓ.ም በሚካሄደው የኮንግረስ ምርጫ ለሚወዳደሩት ብራድ ሼርማን ድምጽ እንደማይሰጡ ግልጽ መልዕክት እንደሚያስተላልፉም ነው የተገለጸው።
የኒው ጀርዚው የኮንግረስ አባል ቶም ማሊኖውስኪ ከተባባሪ ደጋፊዎቻው ጋር በመሆን ‘ኢትዮጵያ ስታብላይዜሽን ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ አክት’ ወይም ‘ኤችአር 6600’ ረቂቅ ሕግ ለኮንግረስ ያቀረቡት ጥር 27 ቀን 2014 ዓ.ም ነው።
ረቂቅ ሕጉን እንዲያይ የተመራለት የኮንግረስ የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ የካቲት 1 ቀን 2014 ዓ.ም በረቂቅ ሕጉ ላይ ውይይት ካደረገ በኋላ በማግስቱ “የኮንግረስ አባላት የኮንግረስ አፈ ጉባኤ በሚያቀርቡት ጥያቄ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው በማሰማት አዎ ወይም አይደለም” በሚል ድምጽ የሚሰጡበት ስርዓት(ቮይስ ቮት) አማካኝነት ረቂቅ ሕጉ በኮንግረሱ ይታይ ወይስ ማሻሻያ ይደረግበት? በሚለው ጉዳይ ላይ ውሳኔ እንዲሰጥበት ለሕግ አውጪ ምክር ቤቱ መምራቱ የሚታወስ ነው።
ከየካቲት አንዱ የኮሚቴው ውይይት በኋላ በሕጉ ዙሪያ በኮንግረሱ የተላለፈ አዲስ ውሳኔ የለም።
የኒው ጀርዚው ሴናተር ሮበርት ሜኔንዴዝ ‘ኤችአር 6600’ ተጓዳኝ ወይም አጋዥ(ኮምፓኒየን ቢል) የሆነው ‘ኢትዮጵያ ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ ፕሮሞሽን አክት ኦፍ 2021’ ወይም ‘ኤስ.3199’ ከአጋሮቻቸው ጋር በመሆን ለሴኔቱ ያቀረቡት ጥቅምት 25 ቀን 2013 ዓ.ም ነው።
ረቂቅ ሕጉ ለሴኔቱ ሁለት ጊዜ ተነቦ ለሴኔቱ የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ የተመራ ሲሆን፤ኮሚቴው መጋቢት 20 ቀን 2014 ዓ.ም ባደረገው ውይይት በሕጉ ላይ ማሻሻያ በማድረግ ሙሉ ሴኔቱ እንዲመለከተው መምራቱ የሚታወስ ነው።
ሴኔቱ ረቂቅ ሕጉን እ.አ.አ በ2022 ከሚመለከታቸው ረቂቅ ሕጎች አንዱ እንዲሆን ከትናንት በስቲያ ባሳለፈው ውሳኔ ማሳለፉ የሚታወስ ነው።
‘ኤችአር 6600’ በኮንግረስ እንዲሁም ‘ኤስ.3199’ በሴኔት ከጸደቀና ለአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ተመርቶ ከፈረሙበት ሕግ ሆኖ ይወጣል።
በአሜሪካ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ረቂቅ ሕጎቹ እንዳይጸድቁ የኮንግረስ አባላትና ሴናተሮችን በማነጋጋርና ማብራሪያ በመስጠት፣ደብዳቤ በመጻፍና በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ዘመቻ በማካሄድ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።