“የእሳት ቀለበት፤ የሕግ ማስከበር ዘመቻ ንፍቀ መዋዕል” መጽሐፍ ተመረቀ

ጥቅምት 15/2015 (ዋልታ) በመከላከያ ጠቅላይ መምሪያ ባለቤትነት የተዘጋጀና በተለያዩ ጻህፍት የተጻፈው “የእሳት ቀለበት፤ የሕግ ማስከበር ዘመቻ ንፍቀ መዋዕል” የተሰኘው መጽሐፍ ዛሬ ተመርቋል።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመን ጨምሮ የመከላከያ ሰራዊት አባላት፣ የቀድሞ ጦር አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት የተመረቀው መጽሐፉ በታሪክ ባለሙያዎች ዳሰሳ እየተደረገበት ይገኛል።

መፅሐፉ በተለይም በሰራዊቱ ሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመውን አሰቃቂ ድርጊትና የጀግናው መከላከያ ሰራዊትን የሕግ ማስከበር ታሪኮችን በተለያዩ ታሪካዊ ዳራዎች አስደግፎ ይዳስሳል።

ዛሬ የተመረቀው በሶስት ምዕራፎች የተከፋፈለው መጽሐፉ 360 ገፆች ያሉት የመጀመሪያው ቅፅ ሲሆን ቀጣይ ሁለት ቅፆች እንደሚዘጋጁ መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል።

በሌላ በኩል የመከላከያ ሰራዊት ቀን “ስለተሰዋልን ደም እና አጥንት ፣ስለተከፈለልን ህይወት፣ ዘላለማዊ ክብር ለኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት” በሚል መሪ ቃል በፓሽን አካዳሚ ተከብሯል፡፡

በዓሉ የአካዳሚው ሰራተኞች፣ተማሪዎች ፣ የመከላከያ ሰራዊት አባላት እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በተለያዩ ሁነቶች ነው የተከበረው፡፡

በመርሃግብሩ ላይ የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ እንዲፈራ የሀገር ሰላም ወሳኝ እና ቁልፍ ጉዳይ መሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን ለዚህ ደግሞ መከላከያ ሰራዊት እየከፈለ ላለው የህይወት ተጋድሎ ክብር መስጠት ያስፈልጋል ነው የተባለው።

የመከላከያ ሰራዊት ቀን “ህዝባችን የጥንካሬያችን ምንጭ ” በሚል መሪ ሀሳብ በዛሬው ቀን እንደሚከበር መገለፁ ይታወሳል ።