የእስራኤል ካቢኔ በአገሪቱ ያለው የአልጃዚራ ቢሮ እንዲዘጋ በሙሉ ድምፅ ውሳኔ አሳለፈ

ሚያዚያ 27/2016 (አዲስ ዋልታ) የጠቅላይ ሚኒስትር ቢኒያሚን ኔታኒያሁ ካቢኔ አልጃዚራ በእስራኤል ውስጥ እንዳይሰራ የሚያደርግ ውሳኔ በሙሉ ድምፅ አፀደቀ።

ካቢኔው ዛሬ ባደረገው ስብሰባ እስራኤል ከሃማስ ጋር ከገባችበት  ግጭት ጋር በተያያዘ የአገሪቱን ብሔራዊ ፀጥታ አደጋ ላይ በሚጥል መልኩ እየሰሩ ያሉ የውጭ ሚዲያዎችን በጊዚያዊነት እንዲታገዱ ውሳኔ አስተላልፏል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ የትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት “አመፅን የሚያነሳሳው አልጃዜራ ቻነል በኔ በሚመራው መንግስት እስራኤል ውስጥ እንዳይሰራ በሙሉ ድምፅ ወስነናል” ብለዋል።

የእስራኤል ኮሙኒኬሽን ሚኒስትር ትዕዛዙን በፍጥነት ተግባራዊ እንዲደረግ ትዕዛዙን መፈረማቸውን ገልጸዋል። በትዕዛዙም መሰረት የሚዲያ ተቋሙ ሲጠቀምባቸው የነበሩ ልዩ ልዩ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችም ይወረሳሉ መባሉን አልጃዜራ ዘግቧል።

እስራኤል እና አልጃዜራ ጥሩ የሚባል ግንኙነት ያልነበራቸው ሲሆን እስራኤል የሚዲያ ተቃሙን ለሃማስ ያዳላ የሚዲያ ሽፋን ያደርጋል በሚል ትከሰዋለች። የኳታሩ ሚዲያ ተቋም በተደጋጋሚ ክሱን ውድቅ  አድርጓል።

በአሁኑ ወቅት በጋዛ ተገኝተው ግጭቱን ከስፍራው ከሚዘግቡ በጣት ከሚቆጠሩ ሚዲያዎች ውስጥ አልጃዜራ አንዱ ሲሆን በግጭቱ የተጎዱ ሰዎችንና የፈራረሱ ተቋማትን በቀጥታ እያስተላለፈ ይገኛል።

የሚዲያ ተቋሙ ኃላፊዎች  በበኩላቸው በኔታንያሁ የሀሰት ውንጀላ በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ጋዜጠኞቻችንና ቢሯችን ላይ ጉዳት እንዲደርስ የሚያነሳሳ ነው ይከሳሉ።

እስራኤል አልጃዜራን ማገዷ ከሃማስ ጋር የማደራደር ጥረት እያደረገች ካለችው ኳታር ጋር ያላትን የተሻለ ግንኙነት አደጋ ሊጥለው እንደሚችል በመረጃው ተጠቅሷል።

አልጃዚራ ቴሌቪዥን ዋና መቀመጫው ዶሃ ሲሆን በከፊል በኳታር መንግስት የገንዘብ ድጋፍ የሚተዳደር ገለልተኛ  የሚዲያ ተቋም እንደሆነ ይነገራል።