የእስራኤል ፓርላማ ምክትል አፈ-ጉባኤ ኢትዮጵያ ለሰላም ያላትን ቁርጠኝነት አደነቁ

መስከረም 9/2015 (ዋልታ) የእስራኤል ፓርላማ ምክትል አፈ-ጉባኤ ቪ ሀውሰር የኢትዮጵያ መንግስት ለሰላም ያለውን አቋምና ቁርጠኝነት አድንቀዋል፡፡

በእስራኤል የኢትዮጵያ አምባሳደር ረታ አለሙ ከምክትል አፈጉባዔ ሀውሰር ጋር በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ መክረዋል፡፡

በውይይታቸውም አምባሳደር ረታ የኢትዮጵያ መንግስት ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የተጓዘበትን ርቀት ለምክትል አፈ-ጉባኤው አስታውሰው አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ይህንን የሰላም ጥረት የሚያስተጓጉል ሦስተኛ ዙር ጥቃት እና ወረራ መፈጸሙን አስረድተዋል፡፡

አሸባሪው ቡድን በኢትዮጵያ ላይ ያደረሰውን ጥፋት፣ ጉዳትና ውድመት እስራኤል ትገነዘባለች የሚል እምነት እንዳላቸውም አክለዋል፡፡

የእስራኤል ምክትል አፈ-ጉባኤ በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግስት ለሰላም ያለውን አቋምና ቁርጠኝነት እንዲሁም የሀገሪቱን ደኅንነት ለማስጠበቅ እየሰራ ያለውን ስራ እንደሚያደንቁ ተናግረዋል፡፡

አያይዘውም አሸባሪው ቡድን በኢትዮጵያ ላይ ያደረገውን ጥቃት እና ወረራ እንዲሁም ያደረሰውን ጉዳት እንደሚያወግዙ ገልጸዋል፡፡

ባለስልጣናቱ በውይይታቸው የሀገራቱን ሁለትዮሽ እና ዘርፈ ብዙ ግንኙነትን ለማሳደግ መስማማታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል፡፡

በነስረዲን ኑሩ