የእነአብዲ ኢሌ የክስ መዝገብ ተከሣሾች አቅርበውት የነበረው አቤቱታ ውድቅ ተደረገ

የካቲት 3/2014 (ዋልታ) አብዲ መሐመድን ጨምሮ 17 ተከሣሾች የሌሎች ክስ ተቋርጦ የኛ ክርክር የሚቀጥልበት ምክንያት የለም በሚል ባሳለፍነው ማክሰኞ የካቲት 01 ቀን 2014 ያቀረቡት አቤቱታ ውድቅ ተደረገ፡፡

ተከሣሾቹ ከዚህ በኋላ በሚኖር ቀጠሮ ፍርድ ቤት አንቀርብም ባሉት መሰረት 14ቱ ዛሬ ሳይቀርቡ ቀርተዋል፡፡

ሆኖም ችሎቱ ዛሬ የካቲት 03/2014 ዓ.ም ተከሳሾች ለፍ/ቤቱ ያቀረቡትን አቤቱታ መርምሮ ትዕዛዝ ለመስጠት በተያዘው ቀጠሮ መሠረት ቢሰየምም፥ በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ካሉት ሦስት ተከሣሾች ውጭ አብዲ መሀመድ (አብዲ ኢሌን) ጨምሮ በቃሊቲ ማረሚያ ቤት የሚገኙት 14 ተከሣሾች ችሎት አንቀርብም ባሉት መሰረት ሳይቀርቡ ቀርተዋል።

ችሎቱም ተከሣሾች ሌሎች ከእስር ተፈተው እኛ ፍርድ ቤት የምንቀርብበት ምክንያት የለም ሲሉ ወደ ፍርድ ቤት ላለመቅረብ ያቀረቡትን አቤቱታ ከመረመረ በኋላ አቤቱታው የህግ መሰረት የሌለው ነው ሲል ውድቅ በማድረግ በያዘው ቀጠሮ መሠረት የምስክር አሰማም ሂደቱ እንዲቀጥል ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

በዚህም መሰረት ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ህግ ቀሪ ምስክሮችን ለመስማት ለየካቲት 14 ቀን 2014 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ የሰጠ ሲሆን የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ዛሬ ያልቀረቡ 14 ተከሳሾችን በቀጣይ ቀጠሮ እንዲያቀርብም ትዕዛዝ መስጠቱን ከፍትህ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡