የእነኢሌኒ ገብረመድኅን አገር የማፍረስ ሴራ ተጋለጠ

ኅዳር 16/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያዊ ዜግነትን የያዙ ባንዳዎችን ጨምሮ 8 የእንግሊዝ፣ አሜሪካና ሌሎች የአውሮፓ ኅብረት የአሁንና የቀድሞ አምባሳደሮች በኢትዮጵያ ስለሽግግር መንግሥት ምስረታ ሲያሴሩ የሚያሳይ ምስል አፈትልኮ ወጣ፡፡

ከበይነመረብ ውይይቱ ተሳታፊዎች ውስጥ በቅርብ ጊዜ የተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት የአፍሪካ ቅርንጫፍ የኢኖቬሽን ኃላፊ ሆና የተሾመችው ኢሌኒ ገብረመድኅን፣ ኤፍሬም ይስሃቅ እና የሕወሓቱ ብርሃነ ገብረክርስቶስ ይገኙበታል።

ዋልታ በተመለከተው የምስል ማስረጃ ኢሌኒ ‹‹ኢትዮጵያ ከ30 እስከ 40 ዓመት ወደኋላ መመለሷን የሚያሳዩ ትንተናዎች እየተመለከትን ነው ብርሃነ ገብረክርስቶስ (የአሸባሪው ሕወሓት አመራርና የሚያሴሩት የሽግግር መንግሥት እቅድ አውጭ) እንዳሉት ወደ ድንጋይ ዘመን እየተመለሰች ነው፤ አንዱ ተግባር በድኅረ ሽግግር ጊዜው የሚኖረው የመልሶ ግንባታ ጉዳይ ነው…›› በማለት ቀዠቷን ስትገልፅ ትደመጣለች፡፡

አገር የማፍረስ የማይሳካ እቅዳቸውን በዋሽንግተን ዲሲ ማዕከል አድርገው ሲያወሩ የነበሩት እኝህ ኢትዮጵያዊያን ከሃዲዎችና የውጭ ዲፕሎማቶች በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠን መንግሥት በጫና ለማስወገድ ሲመክሩ የነበረበትን መረጃ የተመለከቱ ኢትዮጵያዊያን ተቃውሞና አይበገሬነታቸውን እየገለፁ ይገኛሉ፡፡

በተለይም በቲውተር ዘመቻ እንደእነ ኢሌኒ ገብረመድኅን ያሉትን ባንዳዎች የአገር ክህደት ወንጀል በመግለፅ ሴራቸው እንደማይሳካና የኢትዮጵያ አሸናፊነት እጅግ ቅርብ መሆኑን እየጠቀሱ ናቸው፡፡

ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ጨምሮ ኢትዮጵያዊያን በተለይም ከየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ገለልተኛ መሆንንና በሉኣላዊ አገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባትን የሚከለክለው የተባበሩት መንግሥታት የሥራ ኃላፊው ኢሌኒ ላይ እርምጃ በመውሰድ ገለልተኝነትና ለሁሉ እኩል አገልጋይነቱን እንዲያሳየን ሲሉ እየጠየቁ ነው።