የእንስሳት ህክምና እና ግብርና ኮሌጅ ተማሪዎች አስመረቀ

ሐምሌ 10/2014 (ዋልታ) አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የእንስሳት ህክምና እና ግብርና ኮሌጅ በዘርፉ ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች አስመረቀ።

ዩኒቨርሲቲው ከመጀመሪያ ድግሪ ጀምሮ እሰከ ዶክትሬት ድግሪ ያስተማራቸውን 60 ተማሪዎችን ነው ያስመረቀው።

የኮሌጁ ዲን ሂካ ዋቅቶሌ ኮሌጁ በእንስሳት ህክምና እና ግብርና ዘርፎች ከተመሠረተ ጀምሮ እስካሁን ከ4 ሺሕ 500 በላይ ተማሪዎችን አሰልጥኖ ወደ ማኅበረሰቡ ቀላቅሏል ብለዋል።

የእንስሳት ህክምና እና ግብርናው ዘርፍ ከእንስሳት ህክምና ባሻገር በማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዘርፉ ውስጥ ያለው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ኮሌጁ ከመማር ማስተማር ባሻገር በአከባቢው ላይ እየሰራቸው ያሉ ሥራዎችን ጠቅሰዋል፡፡

የተመረቁ ተማሪዎችም ወደ ማኅበረሰቡ ሲቀላቀሉ የኅብረተሰቡን ችግር ፈቺ በመሆን የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጣሰው ወልደሀና (ፕ/ር) ሀገሪቱ ከዘርፉ ተጠቃሚ እንድትሆን ተመራቂዎች የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት መወጣት እንዳለባቸው አሳበዋል።

አክለውም ዘርፉ ሰፊ የምርምር መድረኮችን መፍጠር የሚችል በመሆኑ ተመራቂዎች ባገኙት እውቀት በመጠቀም የኅበረተሰቡን የእለት እለት ህይወት የሚቀይሩ እና አሁን ሀገሪቷ የጀመረችውን ለውጥ የሚያስቀጥሉ እንዲሁም በምግብ ራሷን ለመቻል እያደረገች ያለውን ጥረት የሚያግዙ የምርምር ሥራዎችን መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

በሚልኪያስ አዱኛ