“የእውነታውን ተገንዘቡ” የኢትዮጵያ ጥሪ

መስከረም 12/2014 (ዋልታ) በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በትክክል በመገንዘብ ዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ ፍትሓዊ እና ሚዛናዊ የሆነ ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጥሪ አቀረቡ።

ከተባበሩት መንግሥታት 76ኛ ጉባኤ ጎን ለጎን ከተለያዩ አገራት መሪዎችና ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር በተናጠል እየመከሩ ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ ከአየርላንድ የውጭ ጉዳይ እና መከላከያ ሚኒስትር ስምዖን ኮቨኒ ጋር መክረዋል።

በሰሜን የአገሪቱ ክፍል አሸባሪው ሕወሓት አጠናክሮ የቀጠለባቸውን እኩይ ጥፋት እና ጥቃቶች ተከትሎ በመንግሥት በኩል በሚወሰዱ እርምጃዎች ላይ በተደጋጋሚ የሚቀርቡ ክሶች መነሻቸው የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ በትክክል ካለመረዳት የመነጨ ነው ብለዋል።

የአሸባሪው ጥፉት በወራት ዕድሜ መነፅር ብቻ የሚመዘን ሳይሆን ባለፉት ዓመታት በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በርካታ ዜጎች ሞት ጀርባ ምክንያት የነበሩ አሸባሪዎችን ሲያደራጅ፣ ሲደግፍ እና ስምሪት ሲሰጥ እንደነበር በዝርዝር አብራርተዋል።

የሰብኣዊ ድጋፍ አሰጣጥን በማመቻቸት ረገድ በመንግሥት ላይ ሚዛናቸውን ያልጠበቁ እና ትክክለኛ ያልሆኑ ክሶች ተደጋግመው እንደሚነሱ አውስተው በመንግሥት በኩል የሚደረገው ሰብኣዊ ድጋፍ በችግሩ ተጎጂ ለሆኑ ወገኖች በሙሉ ተደራሽ ያደረገ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማረጋገጣቸውን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።