የኦሮሚያ ክልል ለ4ኛው ዙር አረንጓዴ አሻራ 4 ነጥብ 76 ቢሊየን ችግኝ ማዘጋጀቱን አስታወቀ

ሰኔ 24/2014 (ዋልታ) የኦሮሚያ ክልል ለ4ኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር 4 ነጥብ 76 ቢሊየን ችግኝ ማዘጋጀቱ አስታወቀ፡፡

ለተከላ የሚሆን መሬት በጂ ፒ ኤስ በመለየት እስካሁንም ተከላ የሚከናወንባቸው 4 ቢሊየን ጉድጓዶች ዝግጁ መሆናቸውን የክልሉ ግብርና ቢሮ የደን ልማትና እንክብካቤ ዳሬይክተር ከተማ አብዲሳ ለዋልታ ገልፀዋል።

በአንዳንድ አካባቢዎች ተከላ ለማካሄድ ዝናቡ ከአፈሩ ጋር በደንብ እስኪጣጣም እየተጠባበቁ መሆናቸውንም የጠቀሱ ሲሆን ዝናብ ባገኙ አካባቢዎች ከተዘጋጁት 4 ነጥብ 76 ቢሊየን ችግኞች መካከል ግማሽ ቢሊየን የሚሆን ችግኝ መተከሉን ተናግረዋል።

የተዘጋጁት ችግኞች ለከብቶች መኖ፣ ለምግብና ለደን ሽፋን የሚውሉ ሲሆኑ ክልሉ በዚህ ዓመት ከወትሮው በተለየ መልኩ ሀገር በቀል ለሆኑና ለምግብነት የሚውሉ ችግኞች ላይ ትኩረት ማድረጉንም ኃላፊው ጠቁመዋል።

የተዘጋጁት ችግኞች አፈርን በንፋስም ሆነ በጎርፍ ከመከላከል አንስቶ የአየር ጠባይ ሚዛንን በመጠበቅ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው የገለፁት ኃላፊው ችግኞቹን ኅብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ በየአካባቢው ለመትከል የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።

የችግኝ ተከላው ወቅትና እና ለተተከሉትም የሚደረገው ክትትል በንቃት መቀጠል እንደሚገባም አሳስበዋል።

በደረሰ አማረ