የኦሮሚያ ክልል ለአብርሆት ቤተ መጽሐፍ 20 ሺሕ መጻሕፍትን አበረከተ

ግንቦት 22/2014 (ዋልታ) የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ለአብርሆት ቤተ መጽሐፍ 20 ሺሕ መጻሕፍትን አበረከተ።

ክልሉ ያበረከታቸው መፃሕፍት የታሪክና ማኅበራዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የተለያዩ ይዘት ያላቸው ናቸው ተብሏል።

የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ጉዳዮች ክላስተር አስተባባሪ አብዱልሀኪም ሙሉ ክልሉ በእውቀት የተገነባ ትውልድ በመፍጠር ሂደት ውስጥ የድርሻውን ለመወጣት መጻሕፍት መለገሱን ተናግረዋል።

መጻሕፍትን የተረከቡት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ሀገር በቀል እውቀቶችና ማንነቶችን ለማወቅ ሁሉም ዜጋ መጻሕፍትን ማበርከት እንደሚገባ ገልጸዋል።

ለትውልድ መቀረጽና አንባቢ ትውልድ ለመፍጠር ሁሉም አካላት መጽሐፍን ማበርከት እንዳለበትና ከዚህም ባለፈ በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ብዙ አብርሆቶች እንዲኖሩን መስራት ይእንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።

በሀገር ብልጽግናን ለማረጋገጥ በተለያዩ መስኮች እውቀት ያለው ትውልድ መፍጠር ያስፈልጋል ሲሉም አክለዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በርክክቡ ወቅት እንደተናገሩት ክልሉ ያደረገው ድጋፍ ቤተ መጽሐፉን በተለያዩ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ለመሙላት ለሚደረገው ጥረት አስተዋጽኦው ከፍተኛ ነው ብለዋል።

“ሚሊዮን መጻሕፍት ለሚሊኒየሙ ትውልድ” በሚል የተጀመረው የመጻሕፍት በማሰባሰብ ዘመቻ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ተብሏል።

በሰለሞን በየነ

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW