የኦዲት ግኝቶች አበረታች የእርምት እርምጃዎች እንደተወሰደባቸው ኮሚቴው ገለጸ

ሰኔ 27/2014 (ዋልታ) በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በፌዴራል ደረጃ የተከናወኑት አብዛኛዎቹ የኦዲት ግኝቶች አበረታች የእርምት እርምጃ እንደተወሰደባቸው ገለጸ።

ቋሚ ኮሚቴው የ2014 በጀት ዓመትን የዕቅድ አፈጻጸም አስመልክቶ፣ በበጀት ዓመቱ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤትን የኦዲት ግኝቶች መሠረት አድርጎ ባከናወናቸው የክትትል እና ድጋፍ ሥራዎች በኦዲት ሪፖርቶች የተመላከቱት ግኝቶች የተሻለ የእርምት እርምጃዎች እንደታየባቸው ገልጿል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ክርስቲያን ታደለ የተገኙ ውጤቶች እና በጎ ጅምሮች እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡

ከኦዲት ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በተደረጉት እንቅስቃሴዎች መንስዔም ከዚህ በፊት 14 በመቶ ተመላሽ ይደረግ የነበረው የገንዘብ ምጣኔ አሁን ወደ 40 በመቶ ከፍ ማለቱንም ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ውጤት በመነሳትም ተቋማት የአመራር፣ የክትትል እና ቁጥጥር ሥራቸውን እንዲያሻሽሉ በማድረግ የተሠሩ ሥራዎች መኖራቸውን አንስተዋል፡፡

አያይዘውም ተቋማት በዋናነት የአሠራር ቅልጥፍናቸውን እና የአፈጻጸም ውጤታማነታቸውን በመጨመር ለዜጎች በታለመው ልክ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ተደራሽ ማድረግ አለባቸው ብለዋል፡፡

ከተጠያቂነት አንጻር የተጀመሩ በጎ ጅምሮች ቢኖሩም ቋሚ ኮሚቴው በሰጠው አቅጣጫ መሠረት በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል ወደ 39 የሚደርሱ ተቋማት የገንዘብ መቀጮ መቀጣታቸው በቂ ባለመሆኑ በቀጣይ ተጠናክሮ የሚሠራበት እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

“ከሕዝብ ሀብት፣ ገንዘብ፣ ጊዜ እና ተጠቃሚነት አንጻር ኃላፊነታቸውን የማይወጡ የሥራ ኃላፊዎች እንዲጠየቁ ያስፈልጋል፡፡ ተቋማት ካለባቸው የኦዲት ግኝት ተላቅቀው የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት ለዜጎች እንዲሰጡ በማስቻል፤ የክትትል እና የድጋፍ ሥራችንን በቀጣይ አጠናክረን እንሠራለን” ክርስቲያን አክለው እንዳስረዱት፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ አራሬ ሞሲሳ ቋሚ ኮሚቴው የአስፈጻሚ ተቋማትን ሪፖርት ከመስክ ምልከታው ጋር በማነጻጸር የተሻለ ውጤት መታየቱን መግለጻቸውን የምክር ቤቱ መረጃ ያሳያል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በዋና ኦዲተር ችግር እንደሚታይባቸው የተለዩትን ተቋማት ትኩረት አድርጎ እየሠራ መቆየቱን እና በቀጣይም ይህንን በማጠናከር ተጠያቂነትን ማስፈን የሚያስችሉ የአሠራር ሥርዓቶችን ዘርግተው የቀጣይ በጀት ዓመት የዕቅዳቸው አካል አድርገው እንደሚሠሩ አስታውቀዋል፡፡