የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተቋማዊ ነጻነትን ተግባራዊ በማድረግ ሂደት ምሁራን የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ

ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር)

ነሐሴ 19/2014 (ዋልታ) የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተቋማዊ ነጻነትን ተግባራዊ በማድረግ ሂደት ውስጥ ምሁራን የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ የትምህርት ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ፡፡

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ነፃነት ተፈፃሚነት ላይ ሁሉም አካላት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተቋማዊ ነጻነት ተግባራዊ መደረግ የተቋማትን የውስጥ አቅም ለማሳደግ ሚናው የጎላ መሆኑን ገልፀዋል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተቋማዊ ነፃነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሲደረግ ተቋማቱ የአመራር፣ አስተዳደር፣ አካዳሚያዊ፣ የሰው ኃይል እንዲሁም የገንዘብና ቁሳዊ ሃብት አስተዳደርን በነፃነት እና በተጠያቂነት ለመምራት እንደሚያስችልም ተናግረዋል፡፡

ለመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ነፃነትን ከተጠያቂነት ጋር የሚሰጥ እና የአስተዳደር ሥርዓት በአግባቡ በመዘርጋት ከመንግሥት አሳሪ አሰራር ደረጃ በደረጃ ተላቀው በነፃነት የሚሰሩበትን ሥርዓት ለመዘርጋት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡

ተቋማዊ ነጻነት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተልዕኳቸውን በተሻለ ሁኔታ ለማሳካት፣ የመምህራንንም ሙያዊ አስተዋጽኦ ለማሳደግ እና ኑሯቸውን ለማሻሻል ትልቅ ሚና ያለው በመሆኑ መንግሥትም በትኩረት የሚሰራበት መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታው መጠቆማቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል።

ተቋማዊ ነጻነት ከመጪው 2015 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መተግበር የሚጀምር ሲሆን በቀጣይ ሁለት ዓመታትም አስር ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ለማድረግ እየተሰራ ነው፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured
ቲዊተር https://twitter.com/walta_info
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!