የክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋ ጭማሪ የሚከለክለውን ደንብ አፀደቀ

ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ

መጋቢት 19/2014 (ዋልታ) የሀረሪ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው ውይይት የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋ ጭማሪ እና ተከራዮችን ማስወጣትን የሚከለክለው ደንብ መርምሮ አፅድቋል።

ምክር ቤቱ ደንቡን ያፀደቀው በአገር ዐቀፍ ደረጃ እየተስተዋለ ያለውን የኑሮ ውድነት እና የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠርና በዜጎች ላይ የሚያሳድረውን ተፅእኖ ለመቀነስ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ነው ተብሏል፡፡

አዋጁ ለሦስት ወራት እንደሚቆይና የንግድ ቦታ ኪራይን እንደማያካትት ተጠቁሟል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ አዋጁ በተለይም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያለው የማኅበረሰብ ክፍል በኑሮ ውድነት ምክንያት እየደረሰበት የሚገኘውን ጫና ለመቀነስ እንደሚያግዝ ገልጸው ለደንቡ ተፈፃሚነት የሚመለከተው ሁሉ የበኩሉን እንዲወጣ አሳስበዋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሚስራ አብደላ በበኩላቸው በክልሉ በተለይ በአሁኑ ወቅት የቤት ኪራይ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ስለመሆኑ አንስተው የአዋጁ ተግባራዊ መሆን ችግሩን ለመቅረፍ እንደሚያግዝ ጠቁመዋል፡፡

የመስተዳድር ምክር ቤቱ አባላት በሰጡት አስተያየትም ለአዋጁ ተፈፃሚነት ሁሉም የበኩሉን መወጣት እና በቅንጅት መንቀሳቀስ ያስፈልጋል ማለታቸውን ከክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡