የክልሉ መንግሥት ለኢድ- አልፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፈ

ሚያዝያ 23/2014 (ዋልታ) የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ለመላው የእስልምና ኃይማኖት ተከታዮች ለ1ሺሕ 443ኛው ኢድ- አልፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል፡፡

ባሳለፍነው የረመዷን ወር ኢትዮጵያዊ የመተሳሰብ ባህልን ያላሳዩ ሁኔታዎች የተስተዋሉበት፤ የሰው ልጅን ክቡር ሕይወት፣ አካልና ንብረት ያወደሙ ግጭቶች መስተዋላቸው እሙን ቢሆንም ሙእሚን እና ሙእሚናቱ የተፈጠሩ ግጭቶችን በእርቅ፣ በይቅርታና በፍቅር መርህ በመሻገር የቀደመ የአብሮነት እሴቶቻችንን ለማጽናት ላሳያችሁት ቀናዒነት የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የላቀ አክብሮት አለው ሲል በመልዕክቱ ጠቁሟል፡፡

ይህ ወቅት እንደ ሀገር ተፈጥሯዊ እና ሠው ሰራሽ በሆኑ ተከታታይ ቀውሶች እየተደራረቡ የተመላለሱበት ወቅት እንደመሆኑ መጠን የመሻገሪያ መንገዳችንም በእኩልነት የተመሰረተ አንድነት ላይ በምንገነባው ኢትዮጵያዊ ወንድማማችነትና እህትማማችነት መሆኑን ከታሪካዊ ተሞክሯችንም ሆነ ከነባራዊ ሁኔታዎቻችን መረዳት ይቻላል፤ ይገባናልም ተብሏል፡፡

“ስለሆነም በአማራ ክልል የምትገኙ ኢትዮጵያዊ ሙስሊሞች በክልላችን ሠላም፣ ልማት፣ እኩልነት እና ሀገራዊ አንድነትን በሕዝቦች መካከል ለማጽናት እንደ አንድ የሀገር ባለቤት እንደሆነ የህብረተሰብ ክፍል ገደብ የለሽ አስተዋጽዖዋችሁን እንድታበረክቱ እየጠየቅን በዓሉ የመተሳሰብ፣ የሰላም፣ የደስታና የሀሴት ይሁንላችሁ” ሲል ገልጿል፡፡