የክልሉን ህዝብ የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ በስፋት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

ግንቦት 12/2013 (ዋልታ) – የሶማሌ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት ሙስጠፌ ሙሀመድ የክልሉን ህዝብ የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ በስፋት እየተሰራ መሆኑን ገለጹ፡፡

ምክትል ፕሬዝዳንቱ ከ129 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ በፋፈን ዞን ጉርሱምና ጎል ጀኖ ወረዳዎች የተገነባው የጎሬ-ቦራሌ የውሃ ፕሮጀክትን መርቀዋል፡፡

በክልሉ መንግሥት ከለውጡ በኋላ የህዝቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ በርካታ ስራዎች እንደተሰሩ የገለጹት አቶ ሙስጠፌ፣ ቀሪዎቹንም በሂደት ለመመለስ በመሰራት ላይ ይገኛል ብለዋል።

ባለፉት ሶስት አመታት በክልሉ የተከናወኑ የልማት ሥራዎች ከዚህ በፊት እንዳልተከወኑ የጠቆሙት ምክትል ፕሬዝዳንቱ፣ የክልሉ መንግሥት የዛሬውን ፕሮጀክት ጨምሮ በቅርቡም በተለያዩ የክልሉ አከባቢዎች ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶች እንደሚመረቅ ገልጸዋል።

የጎሬ-ቦራሌ የውሃ ፕሮጀክት ግንባታ በአከባቢው የሚገኙ አርብቶ አደርና ከፊል አርሶ አደር የሆኑ በ13 ቀበሌዎች ከ57 ሺህ በላይ ዜጎችና ከ88 ሺህ በላይ እንስሳትን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተገልጿል።

የሶማሌ ክልል ውሃ ልማት ቢሮ ኃላፊ አብዱራህማን አህመድ በበኩላቸው፣ ፕሮጀክቱ ከ35 ኪ.ሜ በላይ የተዘረጋ እንደሆነና በሁለት አመት ጊዜ ውስጥ ግንባታው እንደተከናወነ ገልፀው፣ በጉርሱምና ጎልጀኖ ወረዳዎች ስር የሚገኙ 13 ቀበሌዎች የሚኖሩ ዜጎች በዘላቂነት ከፕሮጀክቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የክልሉ ውሃ ቢሮ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

አክለውም ፕሮጀክቱን በሙሉ የቴክኒክ እና የአስተዳደር ስራውን የሚሰሩ የአከባቢውን ወጣቶች ቢሮው በማሰልጠን ላይ እንደሆነ በመግለፅ ህብረተሰቡ የተከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶችን እንዲጠብቁ አሳስበዋል።

በምረቃ ሥነ ስርዓቱ የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት ሙስጠፌ ሙሀመድን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የአከባቢው ማህበረሰብና የሀገር ሽማግሌዎች መገኘታቸውን ከሶማሌ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።