የክልሉን የተፈጥሮ ሀብት የሚያለሙ ኢንተርፕራይዞች በስፋት እንዲሰማሩ ጥሪ ቀረበ

ግንቦት 1/2014 (ዋልታ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ያለውን የተፈጥሮ ሀብት በማልማት ለሃገር ምጣኔ ሃብት እንዲያውል ኢንተርፕራይዞች በዘርፉ በስፋት እንዲሰማሩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሌ ሀሰን ጥሪ አቀረቡ።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ያዘጋጀው ስልጠና ዛሬ በአሶሳ ከተማ ሲጀመር  ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት፤ ክልሉ በተለይ ለግብርና ኢንቨስትመንት የሚውል በቂ መሬትና በርካታ ወንዞች አሉት።

በወርቅ፣ እምነበረድ እና በሌሎችም የተፈጥሮ ሃብቶች ክልሉ መታደሉን ገልጸው፤ ኢንተርፕራይዞች በዘርፉ ቢሰማሩ ራሳቸውን ከመጥቀም አልፈው ለአገር ኢኮኖሚ የላቀ አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

ኢንተርፕራይዞች በስፋት በዘርፉ እንዲሰማሩ የክልሉ መንግስት ፍላጎት እንደሆነና ድጋፍ እንደሚያደርግ የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የተፈጥሮ ሃብት ይዘን በድህነት መቀጠል የለብንም ብለዋል።

አያይዘውም ኢንተርፕራይዞች በዘርፉ እንዲሰማሩ ለማስቻል የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅበትም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የአሶሳ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ ማሙየ አብደታ ባንኩ ለኢንተርፕራይዞቹ ስልጠና የሚሰጥበት ዓላማ በአገሪቱ የኢንዱስትሪን ዘርፍ በማሳደግ ንቁ እና ስራ ፈጣሪዎችን ለማፍራት መሆኑን ተናግረዋል።

የንግድ ስራ፣ ፋይናንስ አስተዳደር፣ ሰው ሃብት አስተዳደር እና አያያዝን ጨምሮ ሌሎችንም ያካተተ ስልጠና እየተሰጠ እንደሆነ መጠቆማውን የኢዜአ ዘገባ አመላክቷል፡፡