የካቲት 13/2014 (ዋልታ) ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጨት መጀመሩን ምክንያት በማድረግ የተለያዩ የክልል መንግሥታት ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የእንኳን ደስ አለን መልዕክት አስተላልፈዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያዊያን ብርሃን፣ ለአፍሪካ መከታ የመሆኑ ማብሰሪያ ቀን ስለደረስን እንኳን ደስ አለን ብሏል።
የክልሉ መንግሥት “ለእኛ ኢትዮጵያዊያን ይህ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ከመሆኑም በላይ ሀገራችን አሁን ካለችበት ውስብስብ ችግር ይልቅ መጪው ጊዜ የኢትዮጵያ ገናናነት፣ ክብር፣ ብልፅግና እና አንድነት ኃያል መሆኑን የሚያመላክት ነው” ሲል ገልጿል።
የጋምቤላ ክልላዊ መንግሥት በበኩሉ የኅዳሴ ግድብ ፕሮጀክት በፈተናዎች ውስጥ አልፎ ኃይል ማመንጨት መቻሉ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ከቆሙ የማያሳኩት ነገር እንደሌለ ማሳያ መሆኑን ጠቅሷል።
ግድቡም እዚህ ደረጃ በመድረሱ ለመላው የክልሉ እና የሀገሪቱ ሕዝቦች የእንኳን ደስ አላችሁ ሲል መልዕክቱን አስተላልፏል።
የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ በደስታ መግለጫቸው የታላቁ የኅዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጨት በመጀመሩ ኢትዮጵያዊያን በአዲስ የብርሃን እና የታሪክ ምዕራፍ ላይ መሆናቸውን የሚያበስር መሆኑን ጠቅሰዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን በበኩላቸው የኅዳሴ ግድብ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ የፈጠረው ደስታ ከጉባ አልፎ ለዓለም ተዳርሷል ብለዋል።
“በክልላችን የታየው ደስታ የኢትዮጵያችን ነው፤ እንኳን ደስ አላችሁ” ሲሉም አክለዋል።
የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሁመድ የኅዳሴው ግድብ ኤሌክትሪክ ማመንጨት መጀመሩ ለኢትዮጵያዊያን አዲስ ምዕራፍ ነው ብለዋል።
ይህ ስኬት ከአዲሱ የለውጥ አመራር ቁርጠኝነት፣ አርቆ አሳቢነት እና አዲስ የፈጠራ ሐሳቦች ውጭ የሚቻል አይሆንም ነበር ሲሉም አክለዋል።
የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳው ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ በመላው የሀገራችን ሕዝቦች ላብ የተገነባ የአፍሪካ የብርሀን ማማ ነው ብለዋል።
አንድነታችንን ካጠናከርን እና ከተባበርን ድኅነት ታሪክ ይሆናል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ የኢትዮጵያ ክብር እና ዝናዋ ከዚህም በላይ ደምቆ እንደሚታይ እምነቴ የፀና ነው ሲሉም በመልዕክታቸው ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ የኃይል ማመንጨት ሥራ በመጀመሩ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ከንቲባዋ ባስተላለፉት መልዕክት የኢትዮጵያ ታላቁ የኅዳሴ ግድብ ዛሬ ብርሃን መስጠት በመጀመሩ የከተማችን ነዋሪዎች፣ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብና የኢትዮጵያ ወዳጆች በሙሉ እንኳን ደስ አለን ብለዋል፡፡