የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ለ1443ኛው ዐረፋ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

ሐምሌ 1/2014 (ዋልታ) የክልል መንግሥታት ርዕሳነ መስተዳድሮች ለመላው እስልምና እምነት ተከታይ ኢትዮጵያውያን ለ1443ኛው የኢድ አል-አደሃ ዐረፋ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ።

የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ለ1443 ሂጅሪያ የኢድ አል አድሃ በዓል የኢድ አል አድሐ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክቱም ምዕመኑ በዓሉን ሲያከብር የተቸገሩ ወገኖችን በማሰብ ካለው ነገር ላይ በማካፈል ሊሆን እንደሚገባ ተመላክቷል፡፡

የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ በዓልን በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን ሕዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር እርስ በእርሱ መደጋገፍ እና በሃይማኖቶች መካከል ያለው መቻቻል፣ መተባበርና አብሮነት በማጠናከር ሊሆን ይገባል ብለዋል።

በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በክልሉ ሃይማኖታዊ በዓላት ሲከበሩ የእምነት ቦታዎችን በጋራ የማፅዳት እና ሰላምን በጋራ እያስጠበቀ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም በክልሉ ሰላም እንዲጎለብት እና አብሮነትንና ወንድማማችነት እንዲጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመዋል።

የሶማሌ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር ሙሰጠፋ ሙሁመድ ኡመር የኢድ አል-ዓደሃ ዓረፋ በዓል ቀለምና ዘር ሳይለይ ሁሉም የእምነቱ ተከታዮች በአመት አንድ ጊዜ ተሰባስበው የሚያከብሩት ታላቅ በዓል ነው ብለዋል።

በመሆኑም የሀገራችን ሕዝቦች ይህንን ታላቅ በዓል በሚያከብሩበት ጊዜ እንደተለመደው በመረዳዳት፣ በመተዛዘንና አቅመ ደካሞችን በመመገብና በመደገፍ  እንዲያከብሩና እለቱን በደስታ በፍቅር እንዲያሳልፉ መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመለስ አብዲሳ በበኩላቸው ነቢዩ ኢብራሂም የፈጣሪያቸውን ትዕዛዝ እንዳሟሉ ሁሉ የእስልምና መርሕ የሆነውን ሰላምን መስበክ፣ ወንድማዊ ፍቅርን ማባዛት እና አንድነትን ማጠናከር ይገባል ብለዋል፡፡

በልማት እና በጎ አድራጎት ሥራ ላይ በመሰማራት ሃይማኖቱ የሚያዘውን መልካም ነገር ሁሉ መሥራት አንደሚጠበቅም በእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸው አሳስበዋል፡፡

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ፒኤችዲ) በዓሉ በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ ያላቸው ለሌላቸው በማከፈል፣ እርስ በእርስ በመረዳዳት፣ በመተባበር፣ በመተሳሰብ፣ የዕዝነትና የወንድማማችነት እሴት በተግባር የሚገለጽበትና ትልቅ ትርጉም ያለው ኃይማኖታዊ ክብረ በዓል ነው ብለዋል።

በተለይም ወቅቱ ለሀገራችን ሰላምን በማይመኙና ከውስጥም ከውጭም በበቀሉ ጠላቶቻችን ምክንያት በዜጎች መካከል ግጭት በመፍጠር ሀገር የማፍረስ ፍላጎታቸውን ለማሳካት ጥረት በሚያደርጉበት ወቅት የሚከበር በዓል በመሆኑ ለየት ያደርገዋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም በዓሉን ስናከብር ፈተናዎችን ሁሉ በጽናት በማለፍ፣ መልካም ነገር በመፈጸም፣ ለሰላምና ጸጥታ መስፈን የድርሻችንን በመወጣት እንዲሆን ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡