የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ለሰራዊቱ የ75 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረገ

ነሃሴ 5/2013 (ዋልታ) – የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት 75 ሚሊየን ብር የሚገመት የአይነትና የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን አሰታወቀ።

የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ 609 ሰንጋዎችን፣ የቁም እንስሳት ነጋዴዎች ማህበር 38 ሰንጋዎች እና ኢምሪያል ሪል ስቴት 12 ሰንጋዎችን ድጋፍ አድርገዋል።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ ጃንጥራር አባይ አሸባሪውን የህወሓት ቡድን ለመደምሰስ የከተማው ወጣቶች መከላከያ ሰራዊቱን በመቀላቀል፣ ነዋሪዎች ስንቅ በማዘጋጀት እያሳዩት ያለው ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው  በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ከተማ አስተዳደሩ መከላከያ ሰራዊት ህግን ለማስከበር በሚያደርገው  ድጋፍ  ካሁን ቀደም ከሁለት ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ መደረጉን አስታውቋል ሲል ኢፕድ ዘግቧል፡፡

የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ  ዋና ስራ አስፈጻሚ  ሙቀት ታረቀኝ ለመከላከያ ሰራዊት  በአንደ ወር ውስጥ አንድ መቶ 23 ሚሊየን በአይነት፣ በገንዘብና በስንቅ ድጋፍ መደርጉን አስታውሰው፣ ሰሞኑን በተጀመረው የድጋፍ ማሰባሰብ በመጀመሪያው ዙር 12 ነጥብ አምስት ሚሊየን ብር ከዛሬው ጋር በድምሩ 85 ነጥብ ሰባት ሚሊየን ብር ለመከላከያ ሰራዊት ድጋፍ በማድረግ የክፍለ ከተማው ህዝብ ደጀን  መሆኑን  በተግባር እያሳየ ነው ብለዋል።

የሀገርን አንድነት ለመበተን የተነሳውን አሸባሪ ቡድን ለመምታት ለመከላከያ ሰራዊትና ለተሰጥታ ሃይሉ የኋላ ደጅን በመሆን ህብረተሰቡ እያሳየ ያለው ተነሳሽነት በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የኢፌዲሪ መከላከያ ሰራዊት ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሉዊጅ በበኩላቸው አንድነታችን አሸባሪውን በአጭር ጊዜ ለመደምሰስ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው ህዝቡ እያደረገ ላለው ድጋፍ  አመስግነዋል።