የኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስን ጀግንነት የሚዘክር የፎቶግራፍ ኤግዚቢሽን ተካሄደ

ጥር 21/2014 (ዋልታ) ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና ክብር በግንባር ቀደምትነት ተሰልፈው ታላቅ ገድል ከፈፀሙ ጀግኖች መካከል አንዱ የሆኑት ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስን ጀግንነት የሚዘክር የፎቶግራፍ ኤግዚቢሽን በሀዲያ ዞን ሆሳዕና ከተማ ተካሂዷል፡፡

የፎቶግራፍ ኤግዚቢሽኑን በክብር የከፈቱት የሀድያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ማቴዎስ ሎምበሶ “ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ ባደረጋቸው ተጋድሎዎችና በፈጸማቸው  ጀብዶች  በአየር  ሃይል  ታሪክ  ፈጽሞ  የማይዘነጋ  እና  የጀግኖች  ተምሳሌ  ተደርጎ የሚነገርለት ኢትዮጵያዊ ነው” ብለዋል፡፡

ኮሎኔል በዛብህ በኢትዮጵያ አየር ኃይል ታሪክ ታላላቅ ጀብዶችን በመፈፀም ስመ ጥር ከሆኑ ተዋጊ አብራሪዎች መካከል አንዱ ናቸው፡፡

የዚያድባሬ መንግሥት በምስራቅ ኢትዮጵያ ግዙፍ ወታደራዊ ወረራ በፈጸመበት ወቅት ኮሎኔል በዛብህ ታላቅ ገድል ሰርተዋል፡፡

ኮሎኔሉ በኦጋዴን ሐረዋ፣ አይሻ፣ በእኖሜጢ እና በሌሎችም ቦታዎች የሮኬት ናዳ በማውረድ ወራሪውን የሶማሊያ ጦር ባለበት እንዲገታ ከማድረግ ባሻገር 8 የጠላት ታንኮችን ከእነ ምድብተኛው አውድመዋል፡፡

በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅትም ዳግም የእናት አገራቸውን ጥሪ ተቀብለው ታግለዋል፡፡