የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዝ

የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዝ

ነሐሴ 27/2013 (ዋልታ) ባሳለፍነው ሳምንት ከ14/12/2013 ዓ.ም እስከ 20/12/2013 ዓ.ም ድረስ ከ44 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዛቸውን የገቢዎች ሚኒስቴር አሳታወቀ፡፡

የኮንትሮባንድ እቃዎቹ ከሀገር ሊወጡ እና ወደሃገር ሊገቡ ሲሉ የተያዙ ሲሆን፣ የገቢ ኮንትሮባንድ 38 ሚሊየን 964 ሺህ 200 ብር፤ ወጪ ደግሞ 5 ሚሊየን 383 ሺህ 287 ብር፣ በድምሩ የ44 ሚሊየን 347 ሺህ 487 ብር ግምት ያላቸው ናቸው ተብሏል፡፡

ከኮንትሮባንድ ቁሶቹ መካከል የውጭ ሀገራት ገንዘቦች፣ ወርቅ፣ የወርቅ ማውጫ ማሽን፣ የተለያዩ አልባሳት፣ ጫማ፣ ምግብ ነክ፣ የጦር መሳሪያዎች፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ኮስሞቲክስ፣ ሲጋራ፣ ልባሽ ጨርቅ፣ መለዋወጫ፣ የሰው መድሀኒትና ሌሎችም ይገኙበታል ነው የተባለው፡፡

ሚኒስቴሩ ህብረተሰቡ፣ የክልልና የፌደራል የጸጥታ አካላት እንዲሁም የተቋሙ ሰራተኞች ኮንትሮባንድን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚደረገው ጥረት ላደረጉት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ምስጋና ማቅረቡን ከገቢዎች ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡