የኮይሻ ኤሌክትሪክ ኃይል ፕሮጀክት ሰራተኞች ለመከላከያ ሰራዊት ድጋፍ አደረጉ

ጥቅምት 9/2014 (ዋልታ) የኮይሻ ኤሌክትሪክ ኃይል ፕሮጀክት ሰራተኞች 1 ሚሊዮን 51 ሺሕ ብር ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ አድርገዋል።

በፕሮጀክቱ የሰራተኞች ማህበር ሰብሳቢ ተስፋዬ ጥላሁን ሰራተኞቹ ጁንታው በመከላከያ ሰራዊትና በሀገራችን ላይ የፈጸመውን ክህደት ተከትሎ የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርጉ መቆታቸውን አስታውሰዋል።

ሰራተኞቹ ከዚህ ቀደም ከ413 ሺሕ በላይ ገንዘብ ድጋፍ ያደረጉ ሲሆን፣ በዛሬው እለትም ከሁሉም ሰራተኞች የተሰባሰበውን 1 ሚሊዮን 51 ሺሕ ብር የመከላከያ ተወካዮች ተረክበዋል።

የመከላከያ ተወካይ የሆኑት ሻለቃ ታመነ ዘመዴ በዚሁ ወቅት ህዝቡ እያደረገ ያለው ሁለንተናዊ ድጋፍ የሞራል ስንቅ መሆኑን ጠቁመው፣ የሀገራችን ስጋት እስኪወገድ ድረስ ህዝቡ ድጋፉን እንዲያጠናክርና ከመከላከያ ጎን እንዲቆም ጠይቀዋል። የኮይሻ ፕሮጀክት ሰራተኞችንም አመስግነዋል ።

የደቡብ ክልል የመከላከያ ሀብት አሰባሳቢ ዓብይ ኮሚቴ አባልና የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ ተፈሪ አባተ በክልሉ የሚኖሩ ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ከፍተኛ ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸው፣ ይህ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መናገራቸውን ከክልሉ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።