የወደሙ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት ከ80 ቢሊየን ብር በላይ ያስፈልጋል ተባለ

ነሐሴ 6/2014 (ዋልታ) እንደ ሀገር በጦርነትና በተለያዩ ግጭቶች የወደሙ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት ከ80 ቢሊየን ብር በላይ ያስፈልጋል ተባለ።

የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በአፋር፣ አማራ፣ ቤንሻንጉልና ኦሮሚያ ክልል 1ሺሕ 300 ትምህርት ቤቶች ላይ ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል።

እነዚህን ትምህርት ቤቶች ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች በሚገኝ ድጋፍ እንዲሁም መንግስት ባለው አቅም ለመገንባትም የመልሶ ግንባታ ፕሮጀክት ስራ መጀመሩን ገልፀዋል።

ትምህርት ቤቶቹ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሳይሆን የትምህርት ቤት ጥራት መስፈርትን በሚያማሟሉ መልኩ የሚገነቡ መሆናቸውን በመግለፅም እስከ 80 ቢሊዮን የሚገመት ገንዘብ እንደሚያስፈልግም ገልፀዋል።

የስፖርት ማዘውተሪያ፣ የእርሻ መማሪያ ቦታ፣ የአይሲቲ እና የሌሎችም ሙያዎች መማሪያ ቦታዎችን በውስጣቸው የያዙ ዘመናዊ ትምህርት ቤቶችን እንገነባለንም ብለዋል።

እንዲህ ያሉ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባትም ቢያንስ ለአንድ ትምህርት ቤት ከ50 እስከ 60 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ገንዘብ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የትምህርት ቤቶቹ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ተማሪዎች አይማሩም ማለት አይደለም ያሉት ሚኒስትሩ ባለው አቅም ጠጋግነን ትምህርታቸውን እንዲማሩ የቁሳቁስ ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል።

ትዕግስት ዘላለም (ከጭፍራ)