የወጣቶች በጎ ፍቃድ መርኃ ግብር አመርቂ ውጤት ማምጣቱ ተገለጸ

ግንቦት 19/2014 (ዋልታ) “በጎነት ለአብሮነት” በሚል ሀሳብ የተጀመረው የወጣቶች በጎ ፍቃድ መርኃ ግብር አመርቂ ውጤት ማምጣቱን የሰላም ሚኒስቴር ገለጸ።
የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ታዬ ደንደአ በሰጡት መግለጫ ባለፉት ሁለት ዓመታት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳታፊ በሆኑ ወጣቶች የተሰሩ ሥራዎች በርካታ መሆናቸውን ገልጸው ይህም ወጣቱን በአመለካከት እና በሥነ ምግባር እንዲታነጽ ከማድረጉ ባሻገር ብቁ ዜጋን ማፍራት መቻሉን ጠቁመዋል።
በሰላም ሚኒስቴር አስተባባሪነት የሚከናወነው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በክፍያ ሳይሆን በቀና ልብ የሚከወን በጎ ተግባር መሆኑም ተገልጿል።
ወጣቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳታፊ መሆናቸው የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን በማጎልበት የሕዝብን አንድነት ለማሳደግ የጎላ ሚና እንዳለው የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታው ብሔራዊ የወጣቶች በጎ ፈቃድ ማኅበር አገልግሎት ለሀገራዊ መግባባት እና ለዘላቂ ሰላም በሚል በስፋት የሚሰራበት መርኃ ግብር መዘጋጀቱንም ጠቁመዋል።
በሀገሪቱ የሚስተዋሉ ግጭቶችና እና አለመግባባቶችን በመነጋገር በሰላማዊ መንገድ መፍታት በሚቻልበት የአመለካከት ልህቀት ላይ መስራት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።
ሚኒስቴሩ በተሰጠው ኃላፊነት መሰረት በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር በግለሰቦችና ቡድኖች መካከል ሰላም እና መቻቻልን ለማስፈን እየሰራ እንደሚገኝም ነው ያስታወቁት።
በሃኒ አበበ